የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ጣሊያን የ22 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ

By Feven Bishaw

June 13, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ጣሊያን ለተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚውል የ22 ሚሊየን ዩሮ የብድር ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሺዴና የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ ተፈራርመዋል።

ብድሩ የቡልቡላ፣ ቡሬ፣ይርጋለምና ባአከር የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ማጠናከሪያና በፓርኮቹ ዙሪያ ለሚቋቋሙ የገጠር ሽግግር ማዕከላት ግንባታ የሚውል ነው ተብሏል።

የብድር ስምምነቱ ኢትዮጵያና ጣሊያን ያላቸውን የኢኮኖሚ ትብብር የሚያጠናክር መሆኑን ነው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ ያስታወቁት።

የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊጂ ዲ ማዮ በበኩላቸው፥ ስምምነቱ ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት ለማጠናከር እንደምትሻ የሚያሳይ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።