የዩክሬን አጋሮች በሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ አያያዝ ላይ ልዩነት መፍጠራቸው ተሰማ
አዲስ አበባ፣ሰኔ 6፣2014 (ኤፍ ቢሲ) የዩክሬን አጋር በሆኑት አሜሪካ እና ምዕራባውያን መካከል የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻን በተመለከተ ውዝግብ ውስጥ መግባታቸው ተዘገበ፡፡
የዩክሬን አጋር በሆኑ አገሮች መካክል የተፈጠረው ውዝግብ እና አለመግባባት ዩክሬንን ለመደግፍ የተሰባሰቡትን የኔቶ አባል ሀገራት እና ምዕራባውያንን በእጅጉ እየፈተናቸው መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ምዕራባውያን መንግሥታት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረከሚሄደው የዋጋ ግሽበት እና የነዳጅ ወጪ ጋር እየታገሉ መሆኑን ተከትሎ ጣሊያን እና ሀንጋሪን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት ፈጣን የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጠይቀዋል።
በአንፃሩ ዩክሬን፤ ፖላንድ እና የባልካን ሀገራት “የተኩስ አቁም ከተደረገ ሩሲያ የያዘቻቸውን ግዛቶች በማጠናከር እና አቅሟን በመሰብሰብ ተጨማሪ ጥቃት ልትሰነዝር ትችላለች” በማለት የተኩስ አቁም ሀሳብን አጣጥለዋል፡፡
አንድ የዩክሬን ከፍተኛ ባለስልጣን ለሮይተርስ እንደተናገሩት ሩሲያውያን ጦርነቱ አድካሚ መሆኑን ሲናገሩ ተሰምተዋል፣ ስለሆነም በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠን መግባባት ላይ መድረስ እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የሩሲያን መዳከም እንደሚፈልጉ የተናገሩ ሲሆን፥ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ፑቲን በጦር ወንጀል እንዲከሰሱ ነው የሚሹት።
የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው፥ “ኪየቭ የሰላም ስምምነትን መቀበል የለባትም ፤ የጦር መሳሪያዎችን የበለጠ በመታጠቅ ጦርነቱን ማሸነፍ ይኖርባታል” ንው የሚሉት፡፡
ጀርመን እና ፈረንሳይ በአወዛጋቢ አቋማቸው በመቀጠል ፕሬዚዳንት ፑቲንን በቀጥታ ከመግጠም ይልቅ ጦርነቱን እንዳያሸንፍ ለማድረግ በሩሲያ ላይ አዳዲስ ማዕቀቦችን ለመጣል በኔቶ የተቀረፀው እቅድ መተግበር አለበት” የሚል ሀሳብ ነው ያላቸው፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለሮይተርስ በሰጡት ቃለ ምልልስ፥ የጆ ባይደን እና የቦሪስ ጆንሰን አቋም ወደ ቀዝቃዛው ጦርነት የሚያመራ መሆኑን ጠቅሰው፣ በዚህም ከእንግሊዝ እና አሜሪካ በሀሳብ መለያየታቸውን አስረድተዋል፡፡
ጦርነቱ እና ማዕቀቡ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ያስከተለው ከፍተኛ ጫና በዩክሬን አጋር ሀገራት ላይ የፈጠረው ውጥረት በቅርቡ ግልፅ እየሆነ ይመጣል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡