Fana: At a Speed of Life!

ዜጎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ በተሰራው ስራ ያልለማ መሬት ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል- አቶ አሻድሊ ሀሰን

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 6 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዜጎችን ወደ መደበኛ ህይወታቸው ለመመለስ በተሰራው ስራ ባለፉት 2 አመታት ያልለማውን መሬት ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳደሩ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ አንፃራዊ ሰላም በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች፥ አርሶ አደሮች ወደ እርሻ ስራቸው እንዲመለሱና የሜካናይዜሽን ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል፡፡

አሁንም በክልሉ ጊዜያዊ የመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ዜጎች በመደበኛ ህይወታቸው ላይ መሰማራት እንዲችሉ መንግስት ወደ ቀያቸው እንዲመልሳቸው ይጠይቃሉ፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ÷ አንፃራዊ ሰላም በተረጋገጠባቸው አካባቢዎች ዜጎችን የማቋቋም ስራ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የክልሉ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ታረቀኝ ተሲሳ 442 ሺህ ዜጎች ተፈናቅለው መቆየታቸውን፣ ይህ አሃዝም ከአጠቃላይ የክልሉ ህዝብ አንድ ሦስተኛ እንደሆነ ነው የተናገሩት፡፡

እርቅ በመፍጠር፣ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከርና የሕግ ማስከበር ስራዎች መሰራታቸው አንፃራዊ ሰላም ማስገኘቱን የተናገሩት ኮሚሽነሩ፥ አንፃራዊ ሰላም በተረጋገጠባቸው አካባቢዎችም የመልሶ ማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ወደ አማራ ክልል የተፈናቀሉ 50 ሺህ 550 ዜጎች፣ በተጨማሪም 107 ሺህ የሚደርሱ ወደተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችን ወደ ቀያቸው መመለስ እንደተቻለም ገልጸዋል።

ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላልም ነው ያሉት ኮሚሽነር ታረቀኝ፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.