ዳያስፖራው የጀመራቸውን የሀብት ማሰባሰብና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደር ስለሺ በቀለ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜን ኢትዮጵያ በተፈጠረው ግጭት በደረሰው ጉዳት ዳያስፖራው የጀመራቸውን የሀብት ማሰባሰብና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በኒው ዮርክና ኒው ጀርሲ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
የውይይት መድረኩን ያዘጋጀው በኒው ዮርክና ኒው ጀርሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ተስፋ ለኢትዮጵያ ማህበር ሲሆን፥ በመድረኩ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዋሽንግተን የኢፌዴሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንዳሉት፥ በሰሜን ኢትዮጵያ ከተፈጠረው ግጭት ጋር በተያያዘ ሰዎች መፈናቀላቸውን፣ ተቋማት መጎዳታቸውንና የዲፕሎማሲ ጫና መፈጠሩን አውስተዋል፡፡
ከደረሰው ጉዳት አንፃር ሁሉንም በመንግስት አቅም መሸፈን ስለማይቻል ዳያስፖራው የጀመራቸውን የሀብት ማሰባሰብና የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ስራዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
በተመድ የኢፌዴሪ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ በበኩላቸው፥ በኒው ዮርክና ኒው ጀርሲ አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመደገፍ በልዩ ልዩ ዘርፎች ያለመታከት በመስራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ ይኸው ጥረታቸው ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
“በኢትዮጵያ ላይ ይሰነዘሩ የነበሩ የሀሰት ትርክቶችን ተቋቁመን እንደ ሀገር እንድንቀጥል ዳያስፖራው የነበረው አስተዋጽኦ የማይዘነጋ ነው” ሲሉም ተናግረዋል አምባሳደር ታዬ፡፡
ዳያስፖራው በፐብሊክ ዲፕሎማሲና ሀገራዊ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ሁልጊዜም ለዘላቂ ሀገራዊ ጥቅሞች አጋርነቱን እያሳየ እንደሆነ አንስተው፥ ይህ ጥረት ተጠናክሮ ከቀጠለ ዳያስፖራው በሀገራዊ ዕድገት ውስጥ የሚኖረው አሻራ ደማቅ እንደሚሆን ነው የገለጹት።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር መሐመድ እንድሪስ እንዲሁ፥ ያለንበት ሀገራዊ ሁኔታ የሁሉንም ሀገር-ወዳድ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን አመልክተው፥ ዳያስፖራው የሚያደርጋቸው ድጋፎች የአጭር ጊዜና ዘላቂ ሀገራዊ ችግሮችን ሊፈቱ በሚችሉበት አግባብ መቃኘት እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት።
ዳያስፖራው ከሀገሩ ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር እያከናወናቸው ያሉ ሰፋፊ የኢንቨስትመንት ተሳትፎዎች እንደተጠበቁ ሆነው፥ ከዳያስፖራው የሚሰባሰቡ ድጋፎችም ዘለቄታ ያላቸውና የዳያስፖራውን አሻራ በሚያሳይ መልኩ ተፈጻሚ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት የሀብት ማሰባሰቢያ ስትራቴጂ ማዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
ኃላፊዎቹ አክለውም ተስፋ ለኢትዮጵያ ማህበር እያደረገ ያለውን ጥረት በማድነቅ አመስግነዋል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት ለተጨማሪ ድጋፍ የሚሆን ሀብት የማሰባሰብ ስራ ማከናወናቸውንም ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!