በደሴ ከተማ በሕግ ሲፈለጉ የነበሩ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ምክንያት የ5 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ
በደሴ ከተማ በሕግ ሲፈለጉ የነበሩ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ምክንያት የ5 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 6፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ አስተዳደር በቧንቧ ውሃ ክፍለ ከተማ 4ኛ ፓሊስ ጣቢያ በሕግ ሲፈለጉ የነበሩ ታጠቂዎች ይዘውት በነበረውን ቦንብ በፈጸሙት ጥቃት ምክንያት የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን የከተማው ፖሊስ አስታውቋል።
የ4ኛ ፖሊስ ጣቢያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር መንግስቱ አሊ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገሩት፥ ዛሬ ከቀኑ 10:00 ላይ ሕግ ለማሰከበር በተደረገው እንቅስቃሴ በፖሊስ ጣቢያው ቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩ ታጠቂዎች ይዘውት የነበረውን ቦንብ በማፈንዳታቸው የአንድ ፖሊስና አንድ የልዩ ኃይል አባልን ጨምሮ የአምስት ሰዎች ሕይወት አልፎአል።
የደሴ ከተማ አስተዳደር ፓሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አሳምን ሙላት በበኩላቸው፥ መነሻቸውን ከደሴ ዙሪያ ወረዳ ፅድ ገበያ አካባቢ ያደረጉና በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ሲፈለጉ የነበሩ 4“ሽፍቶች” ወደ ደሴ ከተማ በመግባት የተለያዩ ጥፋቶችን ለመሰንዘር ጥረት ያደረጉ መሆኑን ገልጸው፥ ተፈላጊዎቹ በደሴ ከተማ አስተዳደር እና በደቡብ ወሎ ዞን ፓሊስ ኃይል ጥምረት ከቀኑ 10:00 አካባቢ ተይዘው ወደ 4ኛ ፓሊስ ጣቢያ ለምርመራ እንዲገቡ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህ ሂደት በወንጀል ሲፈለጉ የነበሩት 4 “ሽፍቶች” የያዙትን ትጥቅ እንዲያወርዱ ከፖሊስ የተሰጣቸውን መመሪያ ባለመቀበል እና መመሪያውን በመተላለፍ፥ የታጠቁትን ቦንብ አውጥተው በማፈንዳታቸው፥ተፈላጊ ሽፍቶቹን ጨምሮ አንድ የመደበኛ ፓሊስ እና አንድ የልዩ ኃይል አባልን ጨምሮ በአጠቃላይ የ5 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ነው የከተማው ፖሊስ ያስታወቀው።
ከተፈላጊዎቹ አንደኛው ግለሰብ ቆስሎ እጁን ለፖሊስ መስጠቱንም ኮማንደር አሳምን ሙላትን ጠቅሶ የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።
በደሴ ከተማ 4ኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በቁጥጥር ስር መዋሉንም ፖሊስ አስታውቋል።
በከድር መሀመድ