Fana: At a Speed of Life!

በውሃና በለስላሳ ምርቶች ላይ የታዩ አላግባብ የዋጋ ጭማሪዎች ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ተጠየቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 27፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በውሃ እና በለስላሳ ምርቶች ላይ የታዩ አላግባብ የሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ተጠየቀ፡፡

ተሻሽሎ የወጣው የኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ከፀደቀ ወዲህ ለገበያ የሚቀርቡ የውሃ እና የስላሳ ምርቶች ላይ ያለአግባብ ጭማሪ መስተዋሉን ተከተሎ የገንዘብ፣ የገቢዎች እና የንግድ ሚኒስቴር የስራ ሃላፊዎች ከአምራች ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የንግድ ሚኒስቴር ባጠናው ጥናት መሰረትም ኤክሳይስ ታክስ አዋጁ ከወጣ በኋላ ከ6 እስከ 7 ብር ይሽጥ የነበረው ግማሽ ሊትር ውሃ ወደ 9 ብር ማሻቀቡ ተገልጿል።

በሌላ በኩል ከ10 እስከ 12 ብር የሚሸጡ የለስላሳ መጠጦች አሁን ከ15 እስከ 19 ብር በመሸጥ ላይ እንደሚገኙ በጥናቱ ተመላክቷል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፥ የኤክሳይስ ታክስ ዓላማ ከዚህ በፊት በማምረቻ ወጪ ላይ የተመሰረተውን አሰራር በመቀየር ሲፈጠሩ የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመቅረፍ ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን በታክሱ ከማምረቻ ውጭ ወደ ፋብሪካ ማምረቻ ዋጋ መቀየሩን እንደምክንያት በመውሰድ በአንዳንድ ገበያዎች ላይ በተለይም በታሸገ ውሃና ለስላሳ መጠጦች የመሸጫ ዋጋ ላይ አላግባብ የሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች በመታየታቸው ሊታረሙ እንደሚገባ ሚኒስትር ዲኤታው አሳስበዋል፡፡

በተለይም የውሃ ዘርፍ ለማበረታታትና የፕላስቲክ የማሸጊያ አካባቢዎች እንዳይበክሉ ለማድረግ እየተወሰዱ ያሉ መልካም እርምጃዎችን ከግንዛቤ በማስገባት በጣም ዝቅተኛ ኤክሳይስ ታክስ የተጣለበት ዘርፍ ከመሆኑ አንፃር የዋጋ ጭማሪ መኖር የለበትም ተብሏል፡፡

አያይዘውም ዘርፎቹ ያጋጠሟቸው ችግሮች ካሉ በሂደት ከመንግስት ጋር በመሆን ችግሮቹን ለመፍታት በቅርበት መስራት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

የውሃ እና የለስላሳ አምራች ድርጅቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ኢንጅነር ጌትነት በላይ በበኩላቸው፥ በኤክሳይስ ታክስ አዋጅ ምክንያት ምንም አይነት የዋጋ ጭማሪ እንዳልተደረገ ገልጸዋል፡፡

በአንጻሩ በአንድ እሽግ ምርት ላይ 60 ብር ይሸጥ የነበረው 56 ብር እየተሸጠ መገኘቱን ጠቁመው፥ በገበያ ሰንሰለት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በመፈተሸ ማስተካከያ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.