Fana: At a Speed of Life!

ስግብግብነትን እና የውጭ ያልተገባ ጫናን በመጋፈጥ ተሻጋሪ ተቋማትን መገንባት ከቻልን ኢትዮጵያ የብልጽግና መሰረት ትጥላለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ስንፍና አዘል ስግብግብነትን፣ ሥራ ጠል አመለካከትን፣ የሞራል ዝቅጠትን እና የውጭ ያልተገባ ጫናን በመጋፈጥ ተሻጋሪ ተቋማትን መገንባት ከቻልን ኢትዮጵያ የብልጽግና መሰረት ትጥላለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ሰላም፣ የብሔርና የሀገር ጉዳይ፣ የግለሰብና የቡድን መብት፣ የትናንት ታሪክና የትናንት ፈተና፣ ብሄራዊ ጥቅም እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚዛን ችግር ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም አንስተዋል።
ከዚህ ባለፈም ስንፍና አዘል ስግብግብነት፣ የሞራል ዝቅጠት (ቅጥ ያጣ ሌብነት)፣ የውጭ ያልተገባ ጫና (አንድነታችንን ፣ ልማታችንን የሚገዳደር ጉዳይ)፣ ተሻጋሪ ተቋማት መገንባት እና ልማትና ሥራ ጠል አመለካከትን መጋፈጥ ይገባል ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ሰላም፣ የብሔርና የሀገር ጉዳይ፣ የግለሰብና የቡድን መብት፣ የትናንት ታሪክና የትናንት ፈተና፣ ብሄራዊ ጥቅም እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት የሚዛን ችግር ያለባቸው ጉዳዮች መሆናቸውንም አንስተዋል።
ከዚህ አንጻርም የእነዚህን ጉዳዮች ሚዛን ማስተካከልና መጋፈጥ እንደሚገባ ጠቁመው፥ ይህን ማድረግ ከተቻለ ኢትዮጵያ የብልጽግና መሰረት ትጥላለች ነው ያሉት።
ከሌብነት ጋር በተያያዘ በሰጡት ማብራሪያም ዳኞች፣ ዐቃቤ ሕጎች፣ ፖሊስ፣ ኦዲተርና የሃይማኖት ተቋማት ሌቦች ሆነዋል ብለዋል።
እነዚህ ሌብነትን ከማስቀረት ይልቅ እያስፋፉ በመሆኑም ይህን መታገል ይገባል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው መጪው ክረምት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር በንቃት መሳተፍ እንደሚገባም ጥሪ አቅርበዋል።
በክረምቱ ለሰላም እና ለግብርና መስራት ያስፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክረምቱን አላግባብ ማሳለፍ አይገባም ብለዋል።
በክረምቱ ወቅት 13 ነጥብ 3 ሚሊየን ሔክታር ማረስ ከተቻለ ሀገራዊ ዕቅዱን ከበቂ በላይ ማሳካት እንደሚቻል ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህን መጋፈጥ፣ ሌብነትን መታገል እና ሚዛን መጠበቅ ከቻልን በሚቀጥሉት ዓመታት አሁን ካደረግነው በላይ የእዳ ጫና ያጎበጣት ኢትዮጵያን ዕዳዋን ዝቅ ካደረግን የሚፈለገው ለውጥ ይመጣል ብለዋል፡፡
የብልጽግና ምሳሌዎች የሚባሉት አየር መንገድን መጠበቅ፣ መንገድ ማስፋት፣ ልማት ማስፋት፣ የህዳሴ ግድቡን እና የስኳር ፕሮጀክቶችን መጨረስ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወደ ሀገር ውስጥ የምናስገባቸውን ምርቶች መቀነስና በሀገር ውስጥ መተካት፣ የምንሸጠውን ማበራከት፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ መፍጠር እንደሚገባ ተናግረው ይህን ለማድረግም መንግስት ቁርጠኝነቱም፤ ሙከራውም አለ፤ ይህን ለማድረግ የሰላምን አስፈላጊነት በመረዳት ለሰላም በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.