በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የገበያ ጉድለት መሙላት የሚያስችል ሥራ መስራት አለባቸው – አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ የልማት ድርጅቶች የገበያ ጉድለት መሙላት የሚያስችል ሥራ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ አሳሰቡ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከሚገኙ የልማት ድርጅት አመራሮች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ ወቅት አቶ ሽመልስ እንደገለጹት፥ መንግሥት በልማት ዙሪያ ያለውን ፍላጎትና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለይቶ በማወቅ የተናበበ ተግባር መፈጸም አስፈላጊ ነው።
የልማት ድርጅት አመራሮች ከተለመደው አሰራር በመውጣት ለውጤት የሚያበቃቸውን አዲስ አስተሳሰብና ስልት ተግባራዊ እንዲያደርጉም ነው ያሳሰቡት።
ድርጅቶቹ በንግድ ሥርዓት ሞዴል መመራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፥ ውጤታማነት ላይ ማተኮር ይገባቸዋል ነው ያሉት።
በተለይም ዘመናዊ ቴክኖሎጂንና ፈጠራን በመጠቀም ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አሰራርን መከተል አለባቸው ብለዋል።
ይህ ሲሆን የልማት ድርጅቶቹ የገበያ ጉድለትን መሙላት የሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚደርሱ ነው የገለጹት።
ይህ ብቻ ሳይሆን እነዚህ የልማት ድርጅቶች ግልጽ የሆነ የንግድ ሥራ እቅድ አዘጋጅተው መመራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
ድርጅቶቹ ሁል ጊዜ አዳዲስ አሰራሮችን ወደ ገበያ በማምጣት ጎልተው መታየት እንዳለባቸው መግለጻቸውንም ኢዜአ ዘግቧል።
በእንደዚህ አይነት መልኩ የሚመሩ ከሆነ ከአገር ውስጥ አልፈው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑም አክለዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!