የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንገደኞች አገልግሎት የአፔክስ 2022 ቀጠናዊ ሽልማት አሸነፈ

By Alemayehu Geremew

June 14, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቀጠናው ለመንገደኞች በሚሰጠው የመዝናኛ እና የአውሮፕላን ውስጥ መስተንግዶ ተመራጭ በመሆን የአፔክስ 2022 ሽልማት አሸነፈ፡፡

አየር መንገዱ ከሌሎች መሠል አየር መንገዶች ጋር ተወዳድሮ ሽልማቱን ያሸነፈው ለመንገደኞች በሚያቀርበው ተዝናኖት እንዲሁም ክብካቤን እና ምቾትን ማዕከል ያደረገ አገልግሎት ነው ተብሏል፡፡

የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ በአየርላንድ ደብሊን መካሄዱን የአየር መንገዱ መረጃ ያመላክታል።

በሽልማት ሥነ-ሥርዓቱም ላይ በተለያዩ ሀገራት የሚበሩ አየር መንገዶች ለተሳፋሪዎቻቸው በሚያቀርቡት መስተንግዶ እንደየደረጃቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

የዚህ ዓመት ሽልማት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የተሰጠው 600 በሚደርሱ ባለ 5 ኮከብ ማዕረግ ዓለምአቀፍ አየር መንገዶች ውስጥ ከተሳፈሩ መንገደኞች በተሰበሰበ 1 ሚሊየን የዕርካታ ደረጃ አመላካች ድምፅ ነው፡፡