Fana: At a Speed of Life!

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ከተሞች የዕድገትና ብልጽግና ማሳያ ነፀብራቅ እንድትሆን በመስራት ላይ እንገኛለን – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 7፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) “ከተማችን አዲስ አበባ የሁላችንም ከተማ፣ የሁላችንም ቤት፣ የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ማዕከል እና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ከተሞች የዕድገትና ብልጽግና ማሳያ ነጸብራቅ እንድትሆን ለማስቻል በመስራት ላይ እንገኛለን” ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባዋ ለዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ዕድሳትን ጨምሮ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ያስጎበኙ ሲሆን÷ እድሳቱ ታሪካዊነቱንና ቅርስነቱን በጠበቀ መልኩ እሴት ብቻ በመጨመር  ለሚቀጥሉት ስልሳ ዓመታት እንዲያገለግል ተደርጎ ሥራው መከናወኑን ገልጸዋል፡፡

የማዘጋጃ ቤቱ የቀድሞ ገጽታ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ የማይመች እንደነበር አስታውሰው÷ የዕድሳት ሥራው የቢሮውን ገጽታ ለአገልግሎት ምቹ የሚያደርግና የከተማዋን ዲፕሎማሲ አንድ ደረጃ የሚያሳድግ ነው ብለዋል።

የከተማዋን ዕድገት በዘላቂነት ለማስቀጠል  እና አዲስ አበባ የጋራ ከተማ መሆኗን በተግባር ለማረጋገጥ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች የተሻሉ ግለሰቦችን በከተማዋ የካቢኔ አደረጃጀትና የኃላፊነት ቦታዎች ላይ በመመደብ በባለቤትነት ስሜት በጋራ ለአንድ ከተማና አገር ሁለንተናዊ ዕድገት እየሰራን እንገኛለንም ነው ያሉት፡፡

ከማዘጋጃ ቤት እስከ መስቀል አደባባይ  ያለውን አካባቢ ጨምሮ እስከ ለገሀር የተሰራው የማስዋብ ሥራ በሁሉም ረገድ እይታችንን እያሰፋ የከተማዋን ገጽታ ለመቀየር ብሎም የአገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነውም ብለዋል ከንቲባዋ።

በጉብኝቱ ወቅት ስለ አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ወቅታዊ እንቅስቃሴ፣ የአድዋ 00 ፕሮጀክት የሥራ አፈጻጸም ፣ የተማሪዎች ምገባ፣ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ለመደገፍ የተገነቡ 6 የምገባ ማዕከላትን በሚመለከት ገለጻ አድርገዋል፡፡

በተጨማሪም ጉለሌ የዕደ ጥበብና የሸክላ ሥራን ለማሳደግ የተከፈቱ ማዕከላት እንቅስቃሴን፣ ሸገር ዳቦ፣ የከተማ ግብርና፣ የኑሮ ጫናን ለመቀነስ የተጀመረውን የቅዳሜና እሁድ ገበያ፣ የቤት ፍላጎትና አቅርቦትን ለማጣጣም የሚሰሩ ተገጣጣሚ ቤቶች ግንባታ፣ የአቅመ ደካማ ወገኖች የቤት ዕድሳንና የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በሚመለከት ለዳያስፖራዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ሁሉም በተሰማራበት መስክ ለከተማዋ እና ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል ማለታቸውን ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.