አቶ ደመቀ መኮንን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር እና ከስዊድን ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 8 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሊ እና ከስዊድን ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማቲልዳ ኧርንክራንስ ጋር ተወያዩ።
በውይይታቸው ወቅትም በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ስለሚደረገው ሰብአዊ ድጋፍ፣ በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ከነበረው ግጭት ጋር ተያይዞ ስለተወሰደው ተጠያቂነት እና መተማመን ለመፍጠር በመንግስት በተወሰዱ እርምጃዎች ዙሪያ መክረዋል።
ከዚህ ባለፈም በክላስተር በለማ የስንዴ እርሻ እና በከተማ ግብርና ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
አቶ ደመቀ የዓለም ምግብ ፕሮግራም እና ስዊድን በኢትዮጵያ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ እንዲደርስ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል።
አያይዘውም መንግስት ከአጋሮች ጋር በመሆን ሰብአዊ ድጋፍ ለማድረስ ያለውን ቁርጠኝነት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።
በግጭቱ ወቅት ተፈጽመዋል ከተባሉ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ጉዳዩን የሚከታተል የሚኒስትሮች ኮሚቴ መቋቋሙን አስረድተዋል።
አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በመንግስት በኩል የታሰበውን ሀገራዊው ምክክር እና በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የቀረበውን የሰላም ማዕቀፍ ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።
ህወሓትም ከፀብ አጫሪ ድርጊቱ ሊታቀብና ለሰላም ሂደቱ ተገዢ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በትግራይ ክልል ስላለው የነዳጅና ምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር በተያያዘም ሰብአዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ በዚህ ወቅት ተገልጿል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሊ እና የስዊድን ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማቲልዳ ኧርንክራንስ፥ የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልል ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎቹ በአማራ እና አፋር ክልል በግጭት ምክንያት ለተጎዱ እና በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በድርቅ ለተጎዱ 20 ሚሊየን ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የመንግስት የሰላም ማዕቀፎችን ያደነቁት ከፍተኛ የስራ ሃለፊዎቹ የሰላም መዕቀፎቹ ከኢትዮጵያ አልፈው በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ትልቅ ሚና እንዳላቸው አንስተዋል።