የሶማሌ ክልል ገቢዎች ቢሮ ባለፉት 10 ወራት 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ሰበሰበ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 8፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አሕመድ ሙሁመድ የገቢ አሰባሰቡን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ÷ ባለፉት አሥር ወራት ለመሰብሰብ ከታቀደው 6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር 5 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 88 በመቶ ማሳካት ተችሏል ብለዋል።
በክልሉ የተከሰተው የድርቅ አደጋና የደረሰኝ ግብይት አነስተኛ መሆን ዕቅዱ እንዳይሳካ ማድረጉንም ነው የገለጹት።
ምክትል ቢሮ ኃላፊው አክለውም፤ ከክልሉ ስፋትና ከግብር ከፋዩ ቁጥር ጋር ያልተመጣጠነ የገቢ መሰብሰቢያ ማሽን በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጫና እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸርም÷ የተሰበሰበው ገቢ የ20 በመቶ ብልጫ እንዳለውና በቀሪ ወራት ያልተሳኩ ዕቅዶችን ለማሟላት እየተሠራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!