Fana: At a Speed of Life!

በዘንድሮው የመኸር ወቅት ከአንድ ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት ለማልማት ወደ ሥራ መግባቱን የክልሉ መንግሥት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ሰኔ 8፣2014 (ኤፍ ቢሲ) በዘንድሮው የመኸር ወቅት አንድ ሚሊየን 119 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልላዊ መንግሥት ገልጿል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሪፖርተር እንደነገሩት፥ በክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር ከመደበኛ አርሶ አደሮች በተጨማሪ ባለሀብቶች ሰፋፊ መሬቶችን ወስደው እንዲያለሙና ወጣቶችን በማደራጀት በሜካናይዜሽን እርሻ እንዲሰማሩ እየተደረገ ነው።

በዘንድሮው የመኸር ወቅት በክልሉ አንድ ሚሊየን 119 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት መታቀዱንም ነው የተናገሩት፡፡

ክልሉ ከፍተኛ የመልማት አቅም ቢኖረውም የአቅሙን ያህል እየተጠቀመ እንዳልሆነም ርዕሰ መስተዳደሩ ጠቅሰዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ሀላፊ አቶ ባበከር ኻሊፋ ÷ በክልሉ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እንዲቻል የኩታ-ገጠም እርሻና ሜካናይዜሽን እየተተገበረ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም÷ ዘንድሮ የክልሉ መንግሥት 50 ሚሊዮን ብር ወጭ በማድረግ ትራክተሮችን ገዝቶ ለአርሶ አደሮች አከፋፍሏል ነው ያሉት፡፡

አርሶ አደሮች በበኩላቸው÷ በበጋ የመስኖ ስራዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ በመጪው መኸር የተሻለ ምርት ለማግኘት ዝግጅት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ካለፉት ጊዜያት ጋር ሲነፃፀር በክልሉ አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ የተሻለ ምርት እንዲጠብቁ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል፡፡

በአፈወርቅ እያዩ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.