Fana: At a Speed of Life!

“ስለኢትዮጵያ” የፓናል ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሀዋሳ ከተማ ያዘጋጀው አራተኛው ስለ ኢትዮጵያ የፓናል ውይይት ተጠናቀቀ።

የፓናል ውይይቱ በቱሪዝም ዘርፍ ላይ አተኩሮ የተካሄደ ሲሆን÷ በቱሪዝም ሚኒስትሯ አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ፣ በአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሀት እና በቱሪዝም መስክ ተመራማሪ ዶክተር ፋኑኤል ከበደ የመወያያ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ኢትዮጵያ ያላት ብዝኃነት በራሱ ሀብት መሆኑን ገልጸው÷ እንደ አገር ያለንን የተጋመደ ማንነት ባለመረዳት ኢትዮጵያ ትፈርሳለች በሚል ከውስጥም ከውጭም ያሉ ኃይሎች ቢለፉም ኢትዮጵያ እያሸነፈች ቀጥላለች፤ ትሻገራለችም ብለዋል።

ራዕያችን የበለጸገች ኢትዮጵያን መፍጠር በመሆኑ ይህን ለማሳካት ያለንን የባህልና የቱሪዝም ሀብት አቀናጅቶ መስራት ይገባል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ አንጻር በቱሪዝም መስክ የተወሠኑ የመንግሥት ውሳኔዎች እና በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አገር የሚገነባው በሂደትና በጋራ ነው ያሉት አቶ ደስታ÷ የአገር ግንባታው በአዲስ ዕይታ እና በግልጽ ራዕይ እየተመራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ከተቋቋመ በኋላ ዘርፉን ለማዘመን፣ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ በማጠቃለያ ንግግራቸው ገልጸዋል።

ቱሪዝም ያለው ፋይዳ ከግምት ውስጥ በመግባቱ መንግስት በሚኒስቴር ደረጃ ራሱን አስችሎ እንዳዋቀረው አንስተው÷ የዘርፉን ፖሊሲ የመከለስ ሥራ እየተሰራ መሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ባለድርሻ አካላት ሃሣብ እየሰጡበት በልጽጎ ለአጽዳቂው አካል ለማቅረብ ዝግጅት መጠናቀቁን አብራርተዋል።

ከባህል አንጻር ኢትዮጵያ ሀብታም መሆኗን በመጥቀስ ይህንን ሀብት ወቅቱን ታሳቢ አድርጎ ተግባራዊ በሚሆን ፖሊሲ ጭምር በማስደገፍ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰርጸ ፍሬስብሀት በማጠቃለያ ንግግራቸው አንስተዋል።

ዶክተር ፋኑኤል ከበደ በበኩላቸው÷ የዱር እንስሳት እንደ ሀብት ለሰው ልጅ ካላቸው የጎላ ጠቀሜታ አንጻር የገንዘብ ተመን ሊወጣላቸው ባይችልም ለአካባቢ ጥበቃም ያላቸውን ፋይዳ በአግባቡ ተረድቶ መጠቀም እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

አራተኛው “ስለኢትዮጵያ” የተሰኘው የፎቶግራፍ አውደ ርዕይ በዛሬው ዕለት በሀዋሳ ከተማ መከፈቱን አስታውሶ ኢፕድ ዘግቧል፡፡

በፎቶግራፍ አውደርዕዩ÷ ከ1950ዎቹና 60ዎቹ አንስቶ በየዘመኑ የነበሩ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ሁነቶች ፣ በታሪክ አንጓዎች የተከሰቱ የሕዝብ ጥያቄዎች እንዲሁም ለአገር ሉዓላዊነት የተከፈሉ መስዋዕትነቶችንና ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ሃብቶችጋር ተያያዥነት ያላቸው አንኳር አገራዊ ክንውኖችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ንግግር የተካተቱበት ዐሻራ የተሰኘው መጽሐፍ በሲዳምኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ዛሬ በሀዋሳ ተመርቋል።

ዐሻራ መጽሐፍ በአማርኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ ከዚህ በፊት የተመረቀ ሲሆን÷ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች ተደራሽ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.