Fana: At a Speed of Life!

በጦር መሣሪያ በመታገዝ የዘረፋ ወንጀል የፈፀመው ግለሰብ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ

አዲ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦር መሣሪያ በመታገዝ የዘረፋ ወንጀል የፈፀመው ተከሳሽ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት መቀጣቱን የካፋ ዞን ፍትሕ መምሪያ አስታወቀ።
ተከሳሽ ኦይሰላ ጲላስ ጥቅምት 5 ቀን 2011 ዓ.ም ከቀኑ 7፡00 ሰዓት በካፋ ዞን ዴቻ ወረዳ ሾላ ቀበሌ የግል ተበዳይን በጦር መሣሪያ በመግደል የዘረፋ ወንጀል መፈፀሙን የካፋ ዞን ፍትሕ መምሪያ የክስ መዝገብ አመላክቷል።
ዐቃቤ ሕግ ግለሰቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ ባቀረበው ክስ የግል ተበዳይን በመግደል÷ ስምንት ላሞቹን በመውሰድ የግል ጥቅም ለማግኘት በፈፀመው የወንጀል ድርጊት በከባድ የውንብድና ወንጀል ክስ መስርቶበት ለካፋ ዞን ከፍተኛ ቤት ማቅረቡን የክስ መዝገቡ ያስረዳል፡፡
የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ ያቀረበውን የክስ መዝገብ ሲመለከት ቆይቶ÷ ተከሳሹን ጥፋተኛ ነው ሲል ብይን መስጠቱን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በዚሁ መሠረት የካፋ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 30 ቀን 2014 ዓ.ም ባስቻለው የወንጀል ችሎት÷ ተካሳሽ ኦይሰላ ጲላስ እጁ ከተያዘበት ቀን ጀምሮ በ19 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በሌላ በኩል በሲዳማ ክልል በሙስና ወንጀል የተከሰሰ ተከሳሽ በገንዘብና በጽኑ እስራት ተቀጥቷል፡፡

ተከሳሽ ታደሰ ሪቅዋ የተባለው የቦሪቻ ወረዳ ነዋሪ አላግባብ ጥቅም ለማግኘት ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ሃሰተኛ የባንክ ስሊፕ በመጠቀም 36 ነጥብ 5 ኩንታል ስኳር ከሲዳማ ኤልቶ ገበሬዎች ዩኒዬን ወጪ በማድረግ ለግል ጥቅም አውሏል ተብሏል፡፡

ግለሰቡ የሙስና ወንጀል አዋጅ 881/2007 አንቀጽ 23(3) ላይ የተገለጸውን ህግ በመተላለፉ የሲዳማ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በቀን የካቲት 29 ቀን 2014 ዓ.ም ክስ መስርቶበታል፡፡

በተከሳሽ ላይ የቀረበውን ክስና ክሱን ለማረጋገጥ የቀረቡትን የሰነድና የሰው ማስረጃዎችን ሲያጣራ የቆየው የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰኔ 9 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽን ጥፋተኛ በማለት የሶስት አመት ጽኑ እስራትና የሶስት ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ መወሰኑን ከክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.