በርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ የተመራ ልዑክ ጎዴ ገባ
አዲ አበባ፣ ሰኔ 9፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሀመድ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢስሊ የተመራ ልዑክ ጎዴ ከተማ ገብቷል፡፡
የስዊድን ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ማቲልዳ ኧርንክራንስን እንዲሁም ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችም ተገኝተዋል፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባላት በጎዴ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል፡፡
በጉብኝታቸው ወቅትም ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ÷ ሁሉም ፕሮጀክቶች በጥራትና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ መመሪያ ሰጥተዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ብቻ የጎዴ ከተማ በ800 ሚልየን ብር ወጪ÷ የንፁህ መጠጥ ውሃና ደረጃቸውን የጠበቁ ዘመናዊ የአስፋልት መንገዶች ግንባታ እንዲሁም የጎዴ ሆስፒታል ከፍተኛ ማስፋፊያ ተሰርቶላቸው ለአገልግሎት መብቃታቸው ተመላክቷል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የኡጋዝ ሚራድ ለይሊ ዘመናዊ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታና ሌሎች ትላልቅ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያላክታል፡፡