የሀገር ውስጥ ዜና

የሕግና የፍትሕ ተቋማት አመራሮችን አቅም ለማጎልበት ያለመ የምክክር መድረክ እየተካሄደ ነው

By Shambel Mihret

June 17, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፌደራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲቲዩት የሕግና የፍትሕ ተቋማት አመራሮችን አቅም ለማጎልበት ያለመ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው።

በመድረኩ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልሎችና የሁለቱ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ አቃቢያነ ሕግ ቢሮ ኃላፊዎችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

የፌደራል የፍትሕና የሕግ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ደግፌ ቡላ በመድረኩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር÷ በዜጎች የሚነሱ የፍትሕና የተጠቃሚነት ጥያቄዎችን ለመመለስ የአመራር ብቃት መላቅ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ባለፉት አራት አመታት የህብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የለውጥ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።

በሚፈለገው ልክ ውጤት እንዲመጣ የአመራሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ለዚህም የአመራሩን አቅም ማሳደግ  አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የተቋማት የላቀ ውጤት የሚመዘገበውም አመራሩና ሠራተኛው በሚኖራቸው የጠነከረ ትስስር መሆኑንም ነው የገለጹት።

በመድረኩ የሕግና የፍትሕ ተቋማት አመራሮችን አቅም በማጎልበት ረገድ መከናወን ስለሚገባቸውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት የሚካሄድ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡