ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች እያደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች እያደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል በታንዛኒያ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ጠየቁ፡፡
አምባሳደር ሽብሩ ማሞ በታንዛኒያ የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቃሲም ሱፊ እና ከድርጅታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር በታንዛኒያ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም ፥ በህግ ጥላ ስር ቆይተው የእስር ጊዜያቸውን ያጠናቀቁ ዜጎችን ወደ አገር ቤት ለመመለስ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ድጋፍ አስፈላጊ እንደሆነ አንስተወል።
ኢትዮጵያውያኑ በእስር ቤት ቆይታቸው ሰብዓዊ መብታቸው መጠበቅ እንዳለበት በመጥቀስ በድርጅቱ በኩል አስፈላጊው ሰብዓዊ እንክብካቤ ሊደረግላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
አምባሳደር ሽብሩ ማሞ ድርጅቱ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች እያደረገ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የጠየቁ ሲሆን ፥ እስካሁን ለዜጎች ለተደረገው ድጋፍም ማመስገናቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
የዓለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ቃሲም ሱፊ ፥ አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን 500 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በቅርቡ ከታንዛኒያ ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑን ገልጸው፥ የተቀሩትን ዜጎች ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ሰብአዊ ድርጅቶች ፈንድ በማፈላለግ ወደ ሀገራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንደሚመቻች አብራርተዋል።
ዶክተር ቃሲም ፥ ድርጅታቸው በእስር ላይ ለሚገኙ ዜጎች አስፈላጊውን የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልና በእስር ቤት ቆይታቸው ወቅትም ሰብዓዊ እንክብካቤ እንዲደረግላቸው ከሚመለከታቸው የታንዛኒያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር እንደሚነጋገሩ ገልጸዋል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!