Fana: At a Speed of Life!

በዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ይዘት ኖሯቸው የተለያየ መጠሪያ የያዙ የትምህርት ክፍሎች ስያሜ እንደገና መስተካከል አለበት ተባለ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 10፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ነገር ግን የተለያየ ስያሜ የያዙ ትምህርት ክፍሎች እንደገና ስያሜያቸው ሊስተካከል እንደሚገባ የትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ስያሜ ማስተካከያ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር እያካሄደ ነው፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር አካዳሚክ ጉዳዮች ጄነራል ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ ሚጀና በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ነገር ግን የተለያየ ስያሜ የያዙ ትምህርት ክፍሎች እንደገና ስያሜያቸው ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡
የተለያየ ስያሜ ያላቸው ተመሳሳይ የትምህርት ይዘቶች መስተካከልም÷ በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግር ለመቅረፍ ይረዳል ነው ያሉት፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ዴአ እንደገለጹት÷ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው የቅድመ ምረቃ ስያሜ ማስተካከያ ውይይት ከዚህ ቀደም በዘርፉ የሚስተዋለውን ችግርና ብዥታ ለመቅረፍ ብሎም ለማስወገድ ያግዛል።
ሥርዓተ ትምህርት በዘመነው ዓለም የሰውን ልጅ ወደ ዕድገት ማማ የሚያወጣ መሰላል እንደመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ፈጥኖ መቅረፍ እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ÷ የቅድመ ምረቃ ትምህርት ስያሜ ሲስተካከል ተወዳዳሪና ብቁ የሆነውን ዜጋ ለማፍራት በሚያስችል መልኩና በገበያው ላይ ያለው ተፈላጊነት ታሳቢ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡም ይጠበቃል፡፡
በአበበች ኬሻሞ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.