ከንቲባ አዳነች አቤቤ በየካ ክፍለ ከተማ የተቋቋመውን የምገባ ማዕከል መርቀው ከፈቱ
ከንቲባ አዳነች በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፥ መጀመሪያ ለሰው የሚሆን ነገር ሳይሰራ አገር እቀይራለሁ ማለት አይቻልም፡፡
“እናንተ በቀን አንድ ጊዜ ለመመገብ በምትቸገሩበት አካባቢ እኛ በቀን ሶስት ጊዜ እየበላን መቀጠል የለብንም” ያሉት ከንቲባ አዳነች÷ “የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን የምገባ ማዕከሉን በመክፈቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ የምትቀየረው ሁሉም ሲተባበር እና ኃላፊነቱን ሲወጣ ነው ያሉት ከንቲባዋ÷ ዜጎች በየአካባቢያቸው ወገኖቻቸውን እንዲያስቡም ጠይቀዋል፡፡
በመዲናዋ ያሉ በርካታ ተቋማት የከተማውን ህዝብ ጫና ማቃለል እንዳለባቸው ጠቁመው÷ ለዚህም ሁሉም መስሪያ ቤቶች ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ድርጅት መማር አለባቸው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ድርጅት ከዚህ በፊት የምገባ ማዕከላት ስራ ሲጀመር አንዱን ማዕከል በነፃ በመገንባት አስተዋፅኦ ማበርከቱን ገልጸው፥ ዛሬ የተመረቀው የምገባ ማዕከል ቋሚ ወጪ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሰራተኞችና ኃላፊዎች የወር ደመወዝ መዋጮ የሚቀጥል ይሆናል መባሉን የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡