Fana: At a Speed of Life!

የሰብዓዊ መብት ጥሰት አልደረሰብንም – በኦሮሚያ ክልል በሕግ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ተጠርጣሪዎች

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 11፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል እየተወሰደ ባለው ሕግ የማስከበር እርምጃ በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ተጠርጣሪዎች ሰብዓዊ መብታቸው እንዳልተጣሰ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተሰየመው አጣሪ ቡድን ተናገሩ፡፡
በአቶ ኢሳ ቦሩ የተመራው አጣሪ ቡድን ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል አዳማ፣ መቂ እና ቡራዩ ከተሞች በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን ተመልክቷል፡፡
በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ዜጎች በዚሁ ወቅት ሰብዓዊ መብታቸው አለመጣሱን እንዲሁም የምግብ እና የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ለቡድኑ አባላት አስረድተዋል፡፡
ይሁን እና አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ወደ ፍርድ ቤት እንዳልቀረቡ እንዲሁም የተወሰኑት ደግሞ ከቤተሰቦቻቸው ርቀው የሚገኙ በመሆኑ መቸገራቸውን ጠቁመዋል፡፡
የአጣሪ ቡድኑ አባላት በበኩላቸው÷ በተለይ በመቂ ከተማ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች በቦታ ጥበት እየተቸገሩ በመሆኑ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ለከተማዋ እና ለምሥራቅ ሸዋ ዞን ከፍተኛ አመራሮች ተናግረዋል፡፡
ወደ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ተጠርጣሪዎችም ቀርበው እልባት እንዲያገኙ አቶ ኢሳ ለአካባቢው አመራሮች በሰጡት ግብረ መልስ አሳስበዋል::
በተመሳሳይ የቡራዩ ከተማ ነዋሪዎች መንግስት የጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ እንደሚደግፉ እና የአካባቢያቸውን ሰላም ለማስጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን ለአጣሪ ቡድኑ አስታውቀዋል::
የአጣሪ ቡድኑ አባላትም÷ በአካባቢው ዘላቂ ሰላም እስኪረጋገጥ ድረስ ህብረተሰቡ የጀመረውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.