በመዲናዋ የክረምቱን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ የክረምቱን የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከወዲሁ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡
አስተዳደሩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው÷በአዲስ አበባ ከተማ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰና የንብረት እንዲሁም የሕይወት ስጋት እየሆነ የመጣውን የክረምት ጎርፍ አደጋ ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህ መሰረትም የበለጠ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባሉ ቦታዎችን በመለየት የጎርፍ አደጋ መከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር በመግባት በርካታ ስራዎችን እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተመላክቷል፡፡
በከተማው ለጎርፍ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ቦታዎችን በዝርዝር በመለየት የተለያዩ የቅድመ መከላከል ስራዎች መከናወናቸውንም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ለጎርፍ ተጋላጭ ተብለው ለተለዩ ቦታዎቸ የአጭር እና የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ወደ ተግባር መገባቱን የገለጸው አስተዳደሩ÷ህብረተሰቡም በክረምቱ ለጎርፍ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለየ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
በተጨማሪም ነዋሪዎች ከተማ አስተዳደሩ እንደየአካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ አስፈላጊ ነው ብሎ የሚያምንባቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ሲተገብር ተባባሪ በመሆን ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን በጋራ እንዲከላከሉ አሳስቧል፡፡