ቅዱስ ሲኖዶሱ የተለያየ አመለካካት ያላቸው አካላት ልዩነታቸውን በሰከነ መንገድ እንዲፈቱ አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የተለያየ አመለካካት ያላቸው አካላት የሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ማዕከል ባደረገ መልኩ ልዩነታቸውን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ።
ሲኖዶሱ በሀገራዊ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በዛሬው ዕለት መግለጫ አውጥቷል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫውም ወጣቶች ህዝቡ፣የፖለቲካ ፓርቲዎችና አመራሮች፣ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶችና ሌሎች አካላት ለሀገሪቱ ሰላም መረጋገጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስቧል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች የሰው ህይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙንና በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቤት ንበረታቸው መፈናቀላቸውን በመግለጫው ተመላክቷል ።
ስለሆነም በሀገሪቱ ሰላም እንዲሰፍን የተለየ አመለካካት ያላቸው አካላት ልዩነታቸውን በሰለጠነና በሰከነ መንገድ በውይይት ሊፈቱ ይገባል ነው ያለውቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው።
የሀገሪቱ መጻኢ እድል በወጣቶች ላይ የተጣለ መሆኑን የገለጸው ቅዱስ ሲኖዶሱ፥ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሁሉም ወጣቶች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ህዝብ ለሀገሪቱ አንድነት፣ መከባበርና መፈቃቀር የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጥሪ ቀርቧል።
የመንግስትም ሆኑ የግል የመገናኛ ብዙሃን ድርጅቶች ከተቋቋሙበት መሰረታዊ ተልዕኮ እና ዓላማ አንፃር በተቻለ አቅም ዘርን፣ ቀለምን፣ ብሄርንና ሀይማኖትን መሰረት ካደረጉ የትንኮሳ ቃላት በመራቅ ሚዛናዊ የሆኑ መረጃዎችን ለህዝብ በማቅረብ ለሰላም የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ሲኖዶሱ አሳስቧል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች በሀገሪቱ የቆየውን የአብሮነት እና የአንድነት ባህሏን በሚያጎድፍ መልኩ ላልተገባ ዓላማ እየዋለ ነው ያለው ሲኖዶሱ፥ ዛሬ ላይ የሚደርሰው የህይወት መጥፋት እና ንብረት መውደም ነገ ሁሉንም ቤት ሲያንኳኳ ሁሉም ሰለባ እንደሚሆን በመረዳት ህዝቡ ማህበራዊ ሚዲያዎችን ለሀገራዊ ሰላምና ለአንድነት እንዲጠቀም ነው የጠየቀው።
በየደረጃው ያሉ የፀጥታ እና የፍትህ አካላት ሁሉ በተለያዩ ቦታዎች ግጭትና አለመግባባቶች ከመከሰታቸው በፊት መከላከልን መሰረት ያደረገ የፀጥታ ስራን በመተግበር የሚደርሰውን ጥፋት ለመከላከል የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም አሳስቧል።
መላው ህዝብ እንደየ እምነቱ እና ሃይማኖቱ ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ሶስት ቀናት በፆም እና በፀሎት ለሀገር ሰላም እና አንድነት ለፈጣሪው ጥሪውን እንዲያቀርብ ቅዱስ ሲኖዶሱ ጥሪውን አስተላልፏል።
በድጋፌ ዳኛቸው