የሀገር ውስጥ ዜና

በካምባ ወረዳ አነስተኛ የሃይል ማመንጫ ግድብ ለመገንባት የመሰረተ ድንጋይ ተቀመጠ

By Meseret Awoke

June 19, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 12፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሠ ጫፎና የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ በጋሞ ዞን ካምባ ወረዳ በ7 ሚሊየን ብር ለሚገነባው አነስተኛ የሃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ መሠረተ ድንጋይ አስቀመጡ፡፡

ግንባታው የሚካሄደው በካምባ ዙሪያ ወረዳ ድንጋሞ ቀበሌ ውስጥ በማይጽሌ ወንዝ ላይ ነው፡፡

ለግድቡ ግንባታ የሚሆን በጀት “ክርስቲያን ኤይድ” ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገኘ ሲሆን ለዚህም 7 ሚሊየን ብር መመደቡ ተመላክቷል፡፡

የገጠር ማህበረሰቦችን የሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ የታሰበው ይህ ፕሮጀክት አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከክርስቲያን ኤይድ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር እንደሚገነቡት ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ከ5 እስከ 10 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጨት ይችላል የተባለው ግድቡ ሲጠናቀቅ ከ400 በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ግንባታው በአንድ ዓመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን ፥ ለአካባቢው ማህበረሰብ በርካታ ጥቅሞችን ይዞ እንደሚመጣም ተጠቅሷል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!