ባለፉት 11 ወራት በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር ሊታጣ የነበረው ከ45 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የጉምሩክ ኮሚሽን ባለፉት 11 ወራት በሰራው የህግ ማስከበር ስራ በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበር ኢትዮጵያ ልታጣ የነበረውን 45 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን አስታወቀ፡፡
የጸረ ኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድን ለመከላከል የሚያስችል የውይይት መድረክ በሶማሌ ክልላዊ መንግስት ጅግጅጋ ከተማ በዛሬው ዕለት ተካሂዷል፡፡
በመድረኩ የተገኙት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ ÷ኮሚሽኑ የህግ ተገዥነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ባለፉት 11 ወራት ብቻ 604 ሚሊየን ብር የወጪ እና 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር የገቢ በድምሩ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ባለፉት 11 ወራት በሰራው የህግ ማስከበር ስራ በኮንትሮባንድ እና ንግድ ማጭበርበር ሀገር ልታጣው የነበረውን ከ45 ቢሊየን ብር በላይ ማዳን መቻሉን ነው የገለጹት፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት ህገወጥ ንግድን እና ኮንትሮባንድን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ችግሩ የአገር ደህንነት እና ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ በተቋማት መካከል ያለው ቅንጅታዊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ማለታቸውን ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በውይይት መድረኩ ከጊዜ ወደጊዜ በአፈጻጸም ስልቱ እና በዓይነቱ እየጨመረ የመጣውን ህገወጥ ንግድ እና ኮንትሮባንድን ለመቀነስ ማህበረሰብን መሰረት ያደረገ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ማዘጋጀት ፤ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ የጸጥታ እና የፍትህ ተቋማት ተቀናጅተው መስራት እንደሚገባቸው ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡