የወጣት አደረጃጀቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም 70 ሺህ ወጣቶችን ከሥራ ጋር ያገናኛል- አቶ ንጉሱ ጥላሁን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)የወጣት አደረጃጀቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም በአገሪቱ ከሚገኙ 11 ከተሞች 70 ሺህ ወጣቶችን ከሥራ ጋር እንደሚያገናኝ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ወጣቶች የመጀመሪያ የሥራ ልምድ እና ክህሎት እንዲያገኙ በአዲስ አበባ ከተማ 36 ወረዳዎች ተግባራዊ ለሚደረገው ፕሮግራም ከሁሉም ክፍለከተሞች ለተውጣጡ የወጣት አደረጃጀቶች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ፣ ሥራ ስምሪት እና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራሙ በአገሪቱ ከሚገኙ 11 ከተሞች 70 ሺህ ወጣቶችን ከሥራ ጋር እንደሚያገናኝ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ 49 ሺህ ወጣቶችን ተጠቃሚ የማድረግ ዕቅዱ እንዲሳካ የወጣት አደረጃጀቶች ጉልህ ሚና አላቸው ብለዋል፡፡
የወጣት አደረጃጀቶቹ በተለያየ ምክንያት ከሁለተኛ ደረጃ እና ከዚያ በታች ትምህርታቸውን ያቋረጡ ፣ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 የሆኑ እና ለችግር የተጋለጡ ወጣቶችን የመመልመል እና ልምምድ የሚያደርጉባቸውን ድርጅቶች የማመቻቸት ኃላፊነት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡
በአገራችን የሥራ አጥነት ችግር ከገጠር በበለጠ በከተማ፤ ከከተማም በወጣቶች፣ ከወጣቶችም ትምህርታቸውን ባቋረጡት እና በሴቶች በርትቶ እንደሚታይ በመናገር ይህም ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ብሎም ስነልቦናዊ ችግር የሚያመጣ በመሆኑ የተገኙ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያ ዙር 21ሺህ ወጣቶችን መዝግቦ የማሰልጠን እና ከነዚህ ውስጥ 10 ሺህ 500 ወጣቶችን ለሥራ ልምምድ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ዕቅድ እንዳለው መገለጹን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡