Fana: At a Speed of Life!

በአማራ እና አፋር ክልሎች በጎርፍ አደጋ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ለመከላከል የሚያስችል ስራ እየተከናወነ መሆኑ ተገለፀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ እና አፋር ክልሎች ከዚህ ቀደም በጎርፍ አደጋ አጋጥመው የነበሩ ጉዳቶች እንዳይደገሙ ለማድረግ የሚያስችልና የፈጣን ምላሽ አገልግሎት ለመስጠት የቅድመ ዝግጅት ስራ መሰራቱ ተገለፀ፡፡
 
በዘንድሮው ክረምት በበርካታ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ እና ከባድ ዝናብ ሊዘንብ ይችላል ያለው የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲቲዩት ለጎርፍ ሊጋለጡ ይችላሉ ካላቸው ክልሎች ውስጥ አማራ እና አፋር ተጠቅሰዋል።
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የብሄራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲቲዩት የትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ዳይሬክተር ወይዘሮ ጫሌ ደበሌ÷ የሃምሌ እና ነሐሴ ወራት የዝናብ ቀናቶች የሚበዙባቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ ትንበያው ያሳያል ብለዋል።
 
የኢንስቲቲዩቱ የትንበያ መረጃ እንደሚያሳየው÷
አማራ፣አፋር፣ሶማሌ፣ቤንሻንጉል ጉሙዝ እና ትግራይ ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ ከመደበኛ በላይ ዝናብ ሊዘንብባቸው የሚችሉ አካባቢዎች ናቸው።
ሀረሪ እና ኦሮሚያ ክልሎችእንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር እና የመሳሰሉት አካባቢዎች ደግሞ መደበኛ ዝናብ የሚያገኙ እንደሚሆኑ ነው ወይዘሮ ጫሌ የጠቆሙት።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኢያሱ መስፍን÷ የክረምት ትንበያን መሰረት በማድረግ አስፈላጊውን የቅድመ ዝግጅት ስራ እየሰራን ነው ብለዋል።
 
የአፋር ክልል የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ኩልሱማ ቡራሀባ በበኩላቸው ÷ከዚህ ቀደም በክልሉ በጎርፍ ምክንያት የደረሱ አደጋዎችን መነሻ በማድረግ የቅድመ ጥንቃቄ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።
 
አደጋው ከተከሰተ ደግሞ ፈጣን ምላሽ እና የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጀቶች በሁለቱም ክልሎች መደረጋቸውን ሃላፊዎቹ ተናገረዋል።
 
የብሄራዊ ሚቲዎሎጅ ኢንስቲቲዩት ከመደበኛ በላይ የሚዘንብባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን መደበኛ ዝናብ የሚያገኙት ላይም ጎርፍ ሊከሰት ስለሚችል ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።
 
በዙፋን ካሳሁን
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.