Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችን ማሰልጠን ጀመረ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ግንባታ ተጠናቆ የተመረጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀምሯል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ባይሳ በዳዳ ከፈጠራ ባለሙያዎች ጋር መክረዋል።

የኢንስቲትዩቱ ግንባታ መጠናቀቁን አስመልክቶ ለምረቃ በዓል የሚሆኑ የፈጠራ ሞዴል ስራዎችን የሚያቀርቡ የተመረጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን በተቋሙ ተቀብሎ ድጋፍ በማድረግ ስራዎቻቸውን እንዲያበለጽጉ እየተሰራ ነው፡፡

ዶክተር ባይሳ በውይይቱ  ወቅት እንደገለጹት÷ ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎችን በመስራት በሀሳብ የተጀመረውን ወደ ውጤት በመቀየር በቀጣይ ቅበላ ለሚደረግላቸው የልዩ ተሰጥዖና ተውቦ ተማሪዎች አርዓያ የሚሆኑ ስራዎችን ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

“አይቻልም” የሚባሉ ስራዎች እንደሚቻሉ ማሳየት የምንችልበትን ሂደት በመፍጠር የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ሀብት በመቀየር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ፣ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በማዘመን፣ የስራ እድል በመፍጠርና ከውጪ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በራሳችን በመተካት የድህነትን ጊዜ ልናሳጥር ይገባልም ብለዋል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሂርፓሳ ጫላ÷ የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት መሆን የሚያስችለንን ስራ እንሰራለን ነው ያሉት።

የተቋሙ ስራ መጀመር በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ልዩ ተሰጥዖ ያላቸውን በመሰብሰብ፣ በማብቃት፣ ወደ ውጤት በመቀየርና  የስራ ዕድል በመፍጠር ኢትዮጵያ ያላትን ብዙ የወጣት ኃይል ሀብት መጠቀም የምትችልበትን ስርዓት ይፈጥራል መባሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡

የፈጠራ ባለሙያዎቹ በበኩላቸው÷ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ አቅም ከመፍጠሩም ባለፈ ስራቸውን ወደ ውጤት መቀየር እንደሚያስችላቸው ገልፀዋል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.