የፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰው ሃብት ልማት በጋራ ለመስራት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 14፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የፍትሕ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰው ሃብት ልማት በጋራ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር ጌትነት ታደሰ ስምምነቱን ፈርመውታል።
የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው እንደገለጹት÷ የዐቃቤያነ ሕግ የስራ አፈፃፀምን ለመመዘን መመሪያ ማውጣቱንና ይህንንም ስራ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ፍላጎት ያለው በመሆኑ ስምምነቱ ወሳኝ ነው፡፡
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ አየር መንገድ እገዛ ለማድረግ መስማማቱን ጠቅሰው ከአየር መንገዱ ጋር መስራት ትልቅ ክብር መሆኑንም ተናግረዋል።
ከዚህ አንፃር ተቋሙ ተልዕኮውን በአግባቡ እየተወጣና እቅዶቹን እያሳካ ስለመሆኑ ማረጋገጥና መመዘን እንዳለበትም ነው ያስረዱት፡፡
ከዚህ በፊት የነበረው የስራ መመዘኛ ቢ ኤስ ሲ እንደነበር አስታውሰው÷ የፍትሕ ተቋማት ካላቸው ልዩ ባህሪ አንፃር ውጤቱን ብቻ ሳይሆን የፍትሕ ሂደቱ ጭምር መመዘን እንዳለበት አንስተዋል።
በመሆኑም እንደየስራ ክፍሉ ባህሪ አግባብ ያለው መመዘኛ መዘጋጀቱን ጠቅሰው የውጤት አሞላሉ ፍትሐዊና ተገማች እንዲሆን ብሎም እያንዳንዱ ስራ በየቀኑ እንዲመዘን ያስችላል ብለዋል።
የዛሬው ስምምነትም ለዚህ ስኬት የሚያግዝ መሆኑን ተናግረው በስምምነቱ መሰረት ስራውን ወደ ተግባር እንደሚቀይር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር ጌትነት ታደሰ÷ የሰው ሃብት ልማት፣ ፋይናንስና ግዢ ስርዓትን ለማዘመን አሰራር ዘርግቶ በመጠቀም ከ15 አመት በላይ ልምድ እንዳለው ተናግረዋል።
ልምዱን ለተለያዩ የመንግስት ድርጅቶች እያካፈለ መሆኑን አንስተው በተለይ ደግሞ የሰው ሀብት ልማት ምዘናን በራሱ ባለሙያ አበልፅጎ ለሌሎች እያጋራ ይገኛል ብለዋል።
ፍትህ ሚኒስቴር እድሉን መስጠቱን በማመስገን አሰራሩን በአፋጣኝ ለማድረሰ እንሰራለን ማታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!