Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት 11 ወራት ከወርቅ ምርት 513 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 15፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 11 ወራት ኢትዮጵያ ከወርቅ ምርት 513 ነጥብ 9 ሚሊየን ዶላር ገቢማግኘቷን የማዕድን ሚኒስትሩ ኢጂነር ታከለ ኡማ ገለጹ።

በዚህ ዓመት የወጪ ንግድ ማዕድናትን በሥፋት ፣ በጥራት እንዲሁም በዓይነት በማምረት የተገኘው ገቢ ቡና በመላክ ከተገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠ ዘርፍ መሆኑ ተገልጿል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ÷ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፍቃዶችን ወስደው በገቡት ውል መሠረት ሥራቸውን ያላከናወኑ 972 በማዕድን ምርመራ ፣ ምርት እና ኤክስፖርት ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሐብቶች ህዝብን በሚጎዳ ተግባር ላይ ተሠማርተው በመገኘታቸው ፍቃዳቸው እንዲቋረጥ መደረጉን ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

የማዕድን ሚኒስቴር ÷ ኢትዮጵያ እና ዜጎቿ ከማዕድንና ተፈጥሮ ሐብቶች የሚገባቸውን ያህል እንዲጠቀሙ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎችን በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቁሟል፡፡

የማዕድን ዘርፉ የተለያዩ ሀገራዊ አካባቢያዊ ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ በላቀ ትጋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ የማዕድን ኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የተከናወኑ ሥራዎች ተሥፋ ሰጪ ውጤቶችን እያስመዘገቡ መሆኑንም ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ አመላክተዋል።

በቅድስት ተሥፋዬ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.