ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የሚመጥን አዲስ ሀገራዊ አስተሳስብ ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ብልፅግና ፓርቲ ኢትዮጵያን የሚመጥን አዲስ ሀገራዊ አስተሳሰብ ተግባራዊ ማድረጉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ገለጹ።
ከዛሬ 4 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ሥር የሰደደ የኢኮኖሚ ስብራትና ኢ-ፍትሃዊነት ያየለበት፣ የዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች ጥሰትና አፈና የነገሰበት፣ ጥቂቶች በቡድን ተደራጅተው የሚፈነጩበት ሕወሃት መራሹ ሥርዓት በህዝብ ትግል መለወጡም ነው የተመላከተው፡፡
ሀገራዊ ለውጡ የተከበረችና የታፈረች፣ ዜጎቿን በዕኩልነት ያሰባሰበች ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን በሚገነባና ኢትዮጵያን በሚያፈርስ ቡድን መሃል ግብግብ ገጥሞት እንደነበርም ተነግሯል።
የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አሥፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት ዶክተር አለሙ ስሜ፣ ዶክተር ሰማ ጥሩነህና ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ ÷ በሕዝብ መራር ተጋድሎ የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከለውጡ መባቻ ጀምሮ እልህ አስጨራሽ ትግል እንደተደረገ አውስተዋል።
አሸባሪው ቡድን ሕወሃት በተዛባ ትርክት ክፍፍልና ጥርጣሬን ማናር፣ የማኅበራዊ ዕሴቶች ተጋምዶ መናድ፣ በብሔርና ሃይማኖት ተኮር ግጭቶች ህዝብን ማማረር፣ በመጨረሻም ግልጽ ጦርነት በማወጅ ሀገርን ማፍረስ ላይ ሌት ተቀን ሲሰራ መቆየቱንም ነው ያስታወሱት።
ሀገራዊ ለውጡ ከውስጣዊና ውጫዊ ሰው ሰራሽ ችግሮች ባለፈ በኮቪድ 19፣ በአንበጣ ወረርሽኝ፣ በጎርፍና ድርቅ ተፈጥሯዊ ችግሮችም ክፉኛ ተፈትኖ እንደነበርም አባላቱ አንስተዋል፡፡
በፈተናዎች የታጀበው ሀገራዊ ለውጥ የተሰደዱ እንዲመለሱ፣ የታሰሩት እንዲፈቱ፣ የተዘጉ ሚዲያዎች እንዲከፈቱ፣ የዴሞክራሲ ተቋማት እንዲገነቡና አሳሪ ሕግጋት እንዲሻሻሉ በማድረግ የዴሞክራሲ መሠረት ጥሏልም ነው ያሉት።
ድሕረ ሀገራዊ ለውጡ ቤተኛ እና ተመልካች ሳይኖር ሁሉም የሚሳተፉበት መንግስታዊ ሥርዓት ስለመመስረቱም አንስተዋል።
የቀደመ የሴራ፣ የወዳጅና ጠላት ፖለቲካ የጋራ ሀገር በጋራ የመስራት መንፈስ የተተካበት፣ በነፃና ዴሞከራሲያዊ ምርጫ ህዝባዊ መንግስት የተመሰረተበት፣ ሜጋ ፕሮጀክቶች በተሳካ መልኩ የተከናወኑበትና ጤናማ የፖለቲካ ባህል ግንባታ ዕውን መሆን የተጀመረበት ለውጥ ነውም ብለዋል።
የለውጡ ምክንያት የሆኑ ሀገራዊ ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ስብራቶችን በመጠገን ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የመውሰድ የአንኳር ዓላማ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑንም ገልጸዋል።
ለውጡ የወለደው ብልጽግና ፓርቲም ያለፉ ህፀጾችን በማረም፣ በጎዎችን በማዳበር ኢትዮጵያን የሚመስል ብልጽግና ማርጋገጥና እውነተኛ ዴሞክራሲን መትከል ግብ ይዞ እንደተመሰረተም ነው የተናገሩት።
የፓርቲው አንደኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ቅቡልነት ያለው፣ ሁሉንም ህዝቦች የወከለ ኅብረ ብሔራዊና ወጥ፣ የተደራጀና ጠንካራ ፓርቲ መሆኑን አሳይቷል ብለዋል።
ጉባዔው አገራዊ ለውጡ ስኬቶቹን እየገመገመ የተራመደ፣ የፈተናዎችን ምንጭና መፍትሄ ለይቶ አቅጣጫ ያስቀመጠ ታሪካዊ ጉባዔ መሆኑን ገልጸዋል።
በጉባዔው በተቀመጡ አቅጣጫዎች ላይ በመላ ሀገሪቷ ህዝባዊ ውይይት በማድረግ አቅጣጫዎቹ ከህዝቡ ፍላጎት ጋር የተጣጣሙ ስለመሆኑ ተረጋገጦ ወደ ሥራ መገባቱንም ነው ያነሱት።
በዚህም የህዝብ ጥያቄ የሆነውን ሕግ ማስከበር፣ የአገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር ችግሮች፣ የኑሮ ውድነትን ጨምሮ ማኅበራዊ ችግሮች መፍታት ላይ ማተኮሩን አመላክተዋል።
በዚህም በሕግ ማስክበር ሥራው በተለይም በአማራና ኦሮሚያ ክልልች በጸረ ሰላም ሃይላት ላይ በተወሰደ እርምጃ የዜጎች በሰላም ወጥቶ መግባት መረጋገጡን፣ የኑሮ ውድነት ጫናውን ለመፍታት የተወሰዱ እርምጃዎች ውጤታማ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ከሰሞኑ በምዕራብ ወለጋ በንጹሃን ላይ የጅምላ ግድያ በፈፀመው የሸኔ አሸባሪ ቡድን ላይ መንግስት የተጠናከረ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
ፓርቲው በቀጣይም የህዝብን ሰላምና ደኅንነት የማስጠበቅ፣ ሙስናን የመታገልና የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻል ላይ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
በፖለቲካው መስክ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ወደ ኋላ ያስቀሩ የፖለቲካ ባሕልን በማስቀረት ታፋሪና ተከባሪ የሚያደርግ አዲስ ሀገራዊ አስተሳስብ ዕውን ይሆናልም ብለዋል፡፡
ብዝሃነትን፣ ሕብረ ብሔራዊነትና ሚዛናዊነትን የተቀበለ፣ በፍትሃዊነትና እኩልነት መርህ የሚመራ፣ ለዜጎች መብት ቅድሚያ የሚሰጥና የሀገር በቀል ዕሴቶችን ያካተተ ሥርዓት መገንባት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል።
ውስጠ ዴሞክራሲ ማጎልበት፣ በትምህርትና ሥልጠና በቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የሰለጠነ የሰው ኃይል መገንባት፣ በማኅበራዊ ልማት የጀመራቸውን አመርቂ ውጤቶች ማሥፋት የብልጽግና ፓርቲ ተልዕኮ ነውም ብለዋል።
በአገራዊ አካታች ምክክር የጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ እንዲሰጥ ብልጽግና አቅጣጫ ማስቀመጡን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር ዓለሙ ስሜ ገልጸዋል።
በየወቅቱ በሚያጋጥሙ ፈተናዎች ሳይበገር እንደሚሰራ ገልፀው ህዝቡ ከፓርቲው ጋር በመተባበር ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ለመውሰድ በሚደረገው ጥረት ድጋፉን እንዲያጠናክር ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።