የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመራቸው ተገለጸ

By Meseret Awoke

June 23, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ከተማ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ተዘግተው የነበሩ አገልግሎት ሰጪ የንግድ ተቋማት ሙሉ በሙሉ ስራ መጀመራቸውን የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቲቾት ኩመዳን ፥ የንግዱ ማህበረሰብ ህጋዊ የንግድ ስርዓትን ብቻ በመከተል የተረጋጋ የገበያ ሁኔታ እንዲኖር የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

የፀጥታ ችግሩን ተከትሎ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ግብረ ሃይል ተቋቁሞ የማጣራት ስራ እያደረገ መሆኑን መግለጻቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የተናገሩት ሃላፊው ፥ ህብረተሰቡ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው መረጃ በመስጠት ድጋፉን እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በቢሮው የንግድ ምዝገባና ፍቃድ ዳይሬክተር አቶ ጆን ቾል በበኩላቸው ፥ ሰሞኑን ሸኔ እና ጋነግ የሽብር ቡድኖች በፈጠሩት የፀጥታ ችግር ተዘግተው የነበሩ የንግድ ተቋማት ስራ ላይ መሆናቸውን አንስተዋል።

ያለምንም ኢኮኖሚያዊ ምክንያትና የአቅርቦት ችግር ሳይከሰት ዋጋ ጥማሪ በሸቀጦች ላይ መታየቱን ጠቅሰው ፥ በህገ ወጥ መንገድ ገንዘብ ለማጋበስ የሚሰሩ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!