የሀገር ውስጥ ዜና

ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ ከ138 ሺህ ሜትሪክ ቶን የምግብ ነክ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል ተልኳል – ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን

By Feven Bishaw

June 23, 2022

 

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 16፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ጀምሮ 138 ሺህ 164 ሜትሪክ ቶን የምግብ እና ከ16 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ ክልል መላኩን ብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

 

በዓለም አቀፍ ድርጅቶች አማካኝነት ድጋፍ እየደረሰ እንደሚገኝ እና በዚህም 828 ሺህ 425 ሊትር ነዳጅ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ መደረጉንም አንስተዋል፡፡

የዕርዳታ ቁሳቁሶችን የጫኑ 3 ሺህ 889 ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ተልከው 2 ሺህ 379 ተሽከርካሪዎች ብቻ  መመለሳቸውን እና እስካሁን ድረስ 1 ሺህ 460 ተሽከርካሪዎች አለመመለሳቸውንም ኮሚሽነር ምትኩ በመግለጫቸው ገልፀዋል፡፡

በሌላ በኩል 16 የፌዴራል ተቋማት የሚሳተፉበት ከሳዑዲ ዓረቢያ ዜጎችን የማስመለስ ሥራ ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ከ40 ሺህ በላይ ዜጎች መመለሳቸውን ገልጸው÷ ከእነዚህ ውስጥ 1 ሺህ 562 ተመላሾች ወደ ትግራይ ክልል መሄድ ባለመቻላቸው በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች  ይገኛሉ ብለዋል፡፡

ከክረምቱ ጋር በተያያዘም ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋ ለመከላከል ከተለያዩ ክልሎች ጋር የቅድመ ጥንቃቄ ስራ እየተሰጠ መሆኑንም አቶ ምትኩ ገልጸዋል፡፡

በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች በሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ለተጎዱ ከ19 ነጥብ 5 በላይ ለሆኑ ዜጎች 546 ሺህ 273 ሜትሪክ ቶን የዕለት ደራሽ ምግብ ድጋፍ መደረጉንም የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡