Fana: At a Speed of Life!

ለአርብቶ አደር ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥበት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 17፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአርብቶ አደር ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሰጥበት ዓለም አቀፍ ጉባዔ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል፡፡

በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሚካሄደው ጉባዔ÷ በእንስሳት ሃብት አስተዳደር፣ በአርብቶ አደሩ ላይ የሚከሰቱ ድርቅና የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም በሚቻልበት እና በግጦሽ ልማትና በአርብቶ አደር ችግሮች መፍትሄ ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሁፎች በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ምሁራን ይቀርባሉ።

በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶ/ር ሁሴን ቃሲም ፥ በኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ለእንስሳት ሃብት የሚገባውን ትኩረት እንዳልተሰጠ ጠቁመው ፤ በጉባዔው በአርብቶ አደሩ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ምክረ ሃሳቦች እንደሚቀርቡ ተናግረዋል፡፡

የጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር በሺር አብዱላሂ በበኩላቸው ፥ ዩኒቨርሲቲው በሶማሌ ክልልና በመላ አገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች ላይ የውሃና ግጦሽ እጥረት በሚፈጥርበትና በድርቅ አደጋ ወቅት የአርብቶ አደር ህብረተሰብ ተጋላጭነትን ለመቀነስ እንዲሁም በእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ማሻሻል ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጉባዔው የግብርናና እንስሳት ተመራማሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች፣ የእንስሳትና ተፈጥሮ ሃብት ፖሊሲ አውጪዎች፣ አርብቶ አደሮች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መሳተፋቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.