ዓለምአቀፋዊ ዜና

የአውሮፓ ኅብረት ሩሲያ ላይ ለመዝመት የሚያደርገውን ጥረት በቅርበት እንከታተላለን – ሰርጌይ ላቭሮቭ

By Alemayehu Geremew

June 24, 2022

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 17 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የአውሮፓ ኅብረት እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ሩሲያ ላይ ለመዝመት የሚያደርጉትን “አዲስ ጥምረት” በቅርበት እንደሚከታተሉ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ገለጹ፡፡

ሰርጌ ላቭሮቭ ÷ “ጥምረቱ” ን አዶልፍ ሂትለር ሶቭየት ኅብረትን ከመውረሩ በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር አነጻጽረውታል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በሩሲያ-ዩክሬን መካከል የተከሰተውን ግጭት በመጠቀም ሩሲያ ላይ የተለያዩ ጫናዎችን ለማሳደርና ሉዓላዊነት ለመጋፋት እንደሞከረች መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በወቅቱም አሜሪካ እና አጋሮቿ በሚያደርጉት ጥረት ፍላጎታቸው እንደማይሳካ አስጠንቅቀው ነበር።

በተለያየ ጊዜ አሜሪካ እና አጋሮቿ ለዩክሬን የጦር መሣሪያዎች ድጋፍ ማድረግን ጨምሮ የሩሲያን የባንክና የፋይናንስ ዘርፎች እንዲሁም የአየር መንገድ አገልግሎት እና የጠፈር ኢንዱስትሪዎች ዒላማ ያደረጉ በርካታ ማዕቀቦችን መጣላቸው ተመላክቷል፡፡

ሆኖም ግን ሩሲያ እነዚህን ማዕቀቦች ለመቋቋም የሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት እና ኢኮኖሚዋን ልትደግፍ የምትችልባቸውን የተለያዩ ስልቶች በመቀየስ እየሠራች እንደምትገኝ ሲ ጂ ቲ ኤን እና አር ቲ ኒውስ ዘግበዋል፡፡