Fana: At a Speed of Life!

ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የባቡር የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት የሰረቁ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ለአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር የተዘረጉ የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ የስርቆት ወንጀል ሲፈፅሙ የተገኙ 6 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በአገልግሎቱ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢልቱማ ቂጣታ እንደገለፁት፥ ስርቆቱ የተፈፀመው ከሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ነው፡፡

ስርቆቱ ከተፈፀመባቸው አካባቢዎች መካከልም በተለምዶ መሿለኪያ፣ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፊት ለፊት እና ባምቢስ ወደ ኡራኤል ባለው መንገድ በተዘረጉ የመካከለኛ ቮልቴጅ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ኬብሎች ላይ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡

የተዘረፈው የኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት 1 ሺህ 765 ሜትር የሚሽፍን የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ሲሆን፥ 3 ሚሊየን 829 ሺህ 180 ብር የሚገመት ኪሳራ በተቋሙ ላይ መድረሱንም ገልፀዋል፡፡

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት የአዲስ አበባ ፖሊስ ከፊደራል ፖሊስ እና በአከባቢው በነበሩ የድርጅት ጠባቂዎች ትብብር መሆኑን የገለፁት አቶ ቢሊሱማ ምርምራ እየተካሄደ እንደሚገኝና ሌሎች በዘረፋው የተሳተፉ ግብረ አበሮችን ለመያዝ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በባቡር መሰረተ-ልማት ላይ እየደረሰ ያለው ዘረፋ በከፍተኛ ደረጃ እየተባባሰ መምጣቱ የተገለፀ ሲሆን፥ በ2013 እና በ2014 ዓ.ም ብቻ 29 ሚሊየን 923 ሺህ 255 ብር የሚያወጣ 18 ሺህ 167 ሜትር የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ መዘረፉን ከአዲስ አበባ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.