Fana: At a Speed of Life!

በመተከል ዞን የተገኘውን ሰላም ተከትሎ የህዝብ ለህዝብ እርቀ ሰላም ኮንፍረንሶች ተጠናክረው ቀጥለዋል

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 18፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገርን ሰላም በማይፈልጉ ጸረ ሰላም ሃይሎች አማካኝነት በህዝቦች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ቁርሾ በይቅርታና ምህረት በማለፍ ወደ መደበኛ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ የእርቀ ሰላም ኮንፍረንሶች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

በኮንፍረሱ የተገኙት የክልሉ ሰላም ግንባታና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዮት አልቦሮ፥ ከእርቅ በኋላ ግጭት መፍጠር ከትናንት አለመማር መሆኑን በመገንዘብ የሚካሄዱ እርቀ ሰላም መድረኮች በእውነትና በእምነት ላይ የተመሰረቱ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል።

የህዝቡን የመልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ወስደው ግጭት የሚፈጥሩ ጽንፈኛ ሃይሎችን አጀንዳ ማህበረሰቡ በመገንዘብ አስቀድሞ ሊከላከላቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው፥ “በነበረው አለመረጋጋት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የጉዳቱ ሰለባ መሆናችንን በመገንዘብ መጪውን ጊዜ የጋራ አብሮነትን በማጠናከር ወደ ልማት መግባት ይግባል” ሲሉ አሳስበዋል።

በወረዳው የህግ ማስከበር ስራው ተጠናክሮ በመቀጠሉ ከነባር ቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች መመለሳቸው የተገለፀ ሲሆን፥ ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ወንጀለኞችን አጋልጦ ለህግ ማቅረብ የሁሉንም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተገልጿል፡፡

በድባጢ ወረዳ ጋሌሳ ማዕከል በተደረገው የእረቀ ሰላም ኮንፍረንስ የአማራ ክልል አዋሳኝ ዞንና ወረዳዎችን ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ከ15 ቀበሌ የተወጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች መገኘታቸውን ከመተከል ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.