በሰዎች የመነገድ ድርጊት ለመከላከል የ“ሰማያዊ ልብ” የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግብር ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በሰዎች የመነገድ ድርጊትን ለመከላከል እና በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ጫና መቀነስ የሚያስችል ዓለም አቀፍ የግንዛቤ መፍጠሪያ መርሃ ግበር ተካሄደ።
“ሰማያዊ ልብ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው የግንዛቤ መፍጠሪያ ዘመቻው በዛሬው እለት በሚሌኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።
መርሃ ግብሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደንዛዥ እፅ እና ወንጀል ቢሮ ናቸው በጋራ ያዘጋጁት።
በሰዎች የመነገድ ድርጊት ወይም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ማስቀረት፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተጎዱትን በመንከባከብ ወደ መደበኛ ህይወታቸው መመለስ የመርሃ ግብሩ ዋነኛ ዓላማዎች መሆናቸው ተነግሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደንዛዥ እፅ እና ወንጀል ቢሮ አመራሮችን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
የተቋማቱ እና የድርጅቶቹ ተወካዮች በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በሰዎች የመነገድ ድርጊትን ለመዋጋት እና በህብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ጫና ለመቀነስ ያለመው መርሃ ግብር እስካሁን በኢትዮጵያ በዘርፉ የተሰራውን ስራ በአንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው ብለዋል።
የመርሃ ግብሩ መካሄድም ችግሩን ለመቅረፍ የሚያስችል መሆኑን ነው የተናገሩት።
የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ችግር ከቤት ጀምሮ ሀገር ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ ድርጊቱን በመከላከል የበኩሉን ሚና እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ አካላትም ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል፣ በህገ ወጥ ዝውውር ተጎጂዎችን ለመንከባከብ እና በመሰል መርሃ ግብሮች ላይ በመካፈል ችግሩን ለመዋጋት ቃል ገብተዋል።
በራህዋ መብርሃቱ