Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባ ከ162 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የተከናወነው የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ማሻሻያ ፕሮጀክት ተጠናቀቀ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ የሚስተዋለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ ከ162 ሚሊየን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ሲከናወን የቆየው የማሻሻያና መልሶ ግንባታ ፕሮጀክት የፊዚካል ስራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡
የፕሮጀክቱ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ላቀው እንደገለጹት የመዲናዋ በፍጥነት ማደግና የህብረተሰቡ የኃይል ፍላጎት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ÷ ቀደም ሲል የነበረውን የኤሌክትሪክ መስመር እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
ተቋሙ ፓወር ቻይና ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር የውል ስምምነት በማድረግ የፕሮጀክቱ የሲቪል ግንባታ ሥራ በጥቅምት 2009 ዓ.ም መጀመሩን አንስተዋል፡፡
በዚህም በፕሮጀክቱ 107 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የመሬት ውስጥ ተቀባሪ የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ፣ 69 የመካከለኛ መስመር መቆጣጠሪያ እንዲሁም ከመሬት በላይ 600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
400 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የዝቅተኛ ቮልቴጅ መስመር ዝርጋታ፣ 61 የኮምፓክት ሰብስቴሽን እና 400 ትራንስፎርመር ተከላ መከናወኑንም ነው የገለጹት፡፡
የፕሮጀክቱ አጠቃላይ በጀት 162 ሚሊየን 168 ሺህ 370 የአሜሪካ ዶላር መሆኑን ጠቁመው÷ ከጠቅላላ ዋጋው 15 በመቶ በተቋሙ መሸፈኑንና ቀሪው 85 በመቶ ከቻይና መንግስት ኤግዚም ባንክ የተገኘ ብድር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የፕሮጀክቱ የፊዚካል ሥራ መቶ በመቶ ተጠናቆ በአሁን ወቅት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
ፕሮጀክቱ የተከናወነው ጥራት ባላቸው የኮንክሪት ምሰሶ፣ ሽፍን ሽቦና አስተማማኝ በሆኑ ግብዓቶች በመሆኑ የኤሌክትሪክ መቆራረጥን ከመቀነስ ባሻገር አደጋን ለመቀነስና ለመከላከል የጎላ ሚና እንዳለውም መናገራቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.