በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት መገኘቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በዚህ ዓመት በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች በበጋ መስኖ ስንዴ የተሻለ ምርት ማግኘት መቻሉን የየክልሎቹ ግብርና ቢሮዎች አስታወቁ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ አበራ ወርቁ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ÷ በዚህ ዓመት ከ350 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በበጋ መስኖ ስንዴ መልማቱን ጠቁመዋል።
በዚህም ከ348 ሺህ ሄክታር ያላነሰ ሰብል በመሰብሰብ ከ13 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት መገኘቱን ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃለፊ አቶ ቃል ኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው÷ ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በልዩ ትኩረት በማልማት በበጋ መስኖ ስንዴ እንዲሸፈን ተደርጓል፡፡
እስካሁንም ከ35 ሺህ ሄክታር ላይ የደረሰ ሰብል ተሰብስቦ 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ኩንታል የሚሆን ስንዴ ምርት ተገኝቷል ብለዋል፡፡
ምርቱም በቀዳሚነት በዩኒኖችና በማኅበራት በኩል ገበያው እንዲረጋጋ እንዲሁም ለፋብሪካዎችም ተደራሽ እንዲሆን ተደርጓል ነው ያሉት።፡
በተጨማሪም ለምርጥ ዘር ግብዓትነትም እንደሚጠቀሙበት ነው የገለጹት፡፡
የኢቻ የምግብ ኮምፕሌክስ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ጥላሁን እና የአፍሪካ የምግብ ኮምፕሌክስ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አይሻ ሁሴን በበኩላቸው÷ በሀገራችን ስንዴ በስፋት መመረቱ የተሻለ አምራች እንድንሆን አድርጎናል ብለዋል፡፡
የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ማስቻሉን በመጠቆምም የበጋ ስንዴውን ለፓስታ፣ ለማካሮኒና ለሌሎችም አገልግሎቶች እየተጠቀሙት መሆኑንም ነው የተናገሩት።
በመሀመድ አሊ
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!