Fana: At a Speed of Life!

ባለፉት ዓመታት ሴቶችን ተጠቃሚና በሀገር ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው – የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት ዓመታት ሴቶችን ተጠቃሚ እና በሀገር ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ ለማድረግ የተሠራው ሥራ ውጤት እያመጣ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ተናገሩ፡፡

የብልፅግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ አንደኛ ጉባኤ “የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በሐዋሳ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ባለፉት ዓመታት ሴቶችን ሴቶችን በሀገር ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ፥ ተጠቃሚና ባለቤት ለማድረግ የተሠራው ሥራ ውጤት እያመጣ ነው ብለዋል።

የሴቶችን ብልፅግና ለማረጋገጥ ለሴቶች ብድር በማመቻቸት እና የራሳቸውን ሀብት አፍርተው በሀገር ኢኮኖሚ የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል በርካታ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል፡፡

አቶ አደም ፋራህ ከሴቶች ብልጽግና ፓርቲ 1ኛ ጉባኤ ጎን ለጎን በሰጡት መግለጫ፥ የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መልካም ጅምሮች ቢኖሩም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል፡፡
ሴቶችን በሀገር ጉዳይ ቀዳሚና እኩል ተሳታፊ ለማድረግ እንዲሁም ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ ለማስቻል ፓርቲው ጠንክሮ እንደሚሰሠራም ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ በወለጋ የተከሰተውን ጭፍጨፋ በተመለከተም አካባቢው አሁን ወደ ሰላም እየተመለሰ መምጣቱን ጠቁመው፥ መንግስት ህሕግን በማስከበር የዜጎችን ሰላም ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ማህበረሰቡም የራሱን አካባቢ ሰላም በመጠበቅ የሀገሩን ሰላም ማረጋገጥ አለበት ብለዋል።

የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደገለጹት÷ ሴቶች በሀገር ጉዳይ ላይ ተሳታፊ ከመሆን በተጨማሪ የውሳኔ ሰጪነት ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

በተቀመጡበት የኃላፊነት ቦታ ውጤታማ በመሆን አቅማቸውንም አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ሴቶች ሊግ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መሰረት መስቀሌ በበኩላቸው÷ሴት የብልፅግና ፓርቲ አባላትን ቁጥር ወደ 2 ሚሊየን ማድረስ መቻሉን ገልጸው፥ የትውልድ ግንባታን በማጠናከር የሀገርን ሰላምና አንድነት ማስጠበቅ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

የፖለቲካ ቁማተኞች የሚያደርጉትን እኩይ ተግባር መታገል እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

በጥላሁን ይልማ

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/

ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting

ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/

ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision

ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

 

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.