Fana: At a Speed of Life!

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 7 ሚሊየን ብር የሚያወጡ መሣሪያዎችን በድጋፍ አገኘ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 7 ሚሊየን ብር የሚያወጡ የመረጃ መሰብሰቢያ መሣሪያዎችን ሮያል ኢጂከል ካምፕ ከተሰኘ ተቋም ድጋፍ ማግኘቱን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡

መሣሪያዎቹ የወንዝ ፍሰት መጠንን፣ የከርሰ ምድር ውሃ ከፍታን ፣ የአፈር እርጥበት መጠንን፣ የውሃ ጥራትን እንዲሁም የሜትሮሎጂ መረጃዎችን በመሰብሰብ ወደ ማዕከል በራሳቸው ማስተላለፍ የሚያስችሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

18 መሣሪያዎችን ያስረከቡት የሮያል ኢጂከልካምፕ ተወካይ ሚስተር ኖርበርት ጴጥሮስ÷ ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ያለውን ልምድ ለማካፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይም መሰል ድጋፎችን እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡

ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት÷ መሣሪያዎቹ አስተማማኝ መረጃዎችን ለመሰብሰብና ጥቅም ላይ ለማዋል ያግዛሉ፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ውሃ-ነክ የመረጃ አሰባሰብ ሥርዓቱን ለማዘመን ዕቅድ እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትሩ÷ የሚደረገው ድጋፉ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

ከኔዘርላንድስ የውሃ ባለስልጣንና ሌሎች ተቋማት ጋር በትብብር የሚተገበረው “አካታችነትና ዘላቂነት ላለው ዕድገት ለውሃ ዋጋ የመስጠት” ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ተገኑ ዘርፉ በበኩላቸው ፥ መሣሪያዎቹ ሚኒስቴሩ በውሃ አጠቃቀም፣ በውሃ ፈቃድ፣ ምደባና በውሃ ጥራት ክትትል ረገድ የሚሠራውን ሥራበአስተማማኝ መረጃዎችን ለማሰባሰብና ጥቅም ላይ ለማዋል እንደሚያስችሉ ተናግረዋል፡፡

ከመሣሪያዎቹ አተካከልና አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የቴክኒክ ድጋፍና ለባለሙያዎቹም የአቅም ግንባታ ስልጠና በፕሮጀክቱ አማካይነት እንደሚሰጥም ንው በርክክቡ ወቅት የተገለጸው::

ፕሮጀክቱ በአዋሽ ተፋሰስ ውስጥ ያለውን የውሃ ሀብት አስተዳደር ለማሻሻልና ውጤታማና ፍትሃዊ አጠቃቀም እንዲሰፍን ለማድረግ እንደሚሠራ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.