Fana: At a Speed of Life!

ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አረጋገጡ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ እንደምትቀጥል የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አረጋገጡ።

የኢፌዲሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተላከ ልዩ መልዕክት በዛሬው እለት ለጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ማስረከባቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ ጃፓን ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የልማት ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ጃፓን የጅማ-ጪዳ መንገድን ለመገንባት 9 ነጥብ 7 ቢሊየን የን ድጋፍ ማድረጓን የጠቀሙ ሲሆን፥ በሰው ሃይል አቅም ግንባታና በጂኦ-ተርማል ሃይል ልማት ላይ እገዛ እያደረገች እንደሆነም አውስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግሉ ዘርፍ እንቅስቃሴን ለማበረታታት እየተወሰዱ ያሉ የሪፎርም እርምጃዎች የጃፓን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ኢንቨስት እንዲያደርጉ እንደሚያበረታታም ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ተሸላሚ በመሆናቸውም የተሰማቸውን ደስታ በድጋሚ ገልፀዋል።

ሀጊቢስ በተባለው የአውሎ ንፋስ ሳቢያ በጃፓን በሰውና በንብረት ላይ ደረሰውን ከባድ አደጋ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለላኩላቸው መልዕክትም ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

በነሐሴ ወር በዮኮሃማ በተካሄደው የቲካድ 7 ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመገኘታቸው መደሰታቸውንና ከእርሳቸውም ጋር በጋራ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ላይ የሚመክር ስብሰባ መምራታቸውን አስታውሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሚቀጥለው ዓመት በጃፓን ኦፊሴላዊ ጉብኝት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውንም እንዲሁ አንስተዋል፡፡

የኢፌዲሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ የጃፓን አዲሱ ንጉስ በዓለ ሲመት ላይ ኢትዮጵያን በመወከል ለመሳተፍ ነው ወደ ቶክዮ ያቀኑት።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.