አለመግባባቶችን ሰበብ በማድረግ ጽንፈኛ ኃይሎች የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ለማወክ እየሰሩ መሆኑን ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 23 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አለመግባባቶችን ሰበብ በማድረግ ጽንፈኛ ኃይሎች ከውስጥና ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር በመቀናጀት የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ለማወክ እየሰሩ መሆኑን ፌደራል ፖሊስ ባገኛቸው መረጃዎች አረጋግጧል።
በዛሬው ዕለት የተደረጁ ኃይሎች የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ቢሮን መስታወት በመሰባበር መጠነኛ ጉዳት ማድረሳቸውንም አስታውቋል።
ፖሊስ እነዚህን ኃይሎች በቁጥጥር ስር አውሎ በህግ አግባብ ተጠያቂ እንዲሆኑ ምርመራ እያደረገባቸው መሆኑንም ገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪ ጽንፈኛ ኃይሎች ከውጭ ጠላቶቻችን ጋር ተቀናጅተው የሀገራችንን ጸጥታ ለማደፍረስ የተለያዩ መሣሪያዎችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረጉ እንደሆነም አመላክቷል።
ስለሆነም መላው የሀገራችን ሙስሊም ህብረተሰብ ይህንን ተገንዝቦ የሀገሩንና የሀይማኖቱን ሰላምና ደህንነት እንዳይደፈርስ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ እያሳሰብን፣ ፖሊስ ከድርጊታቸው በማይቆጠቡት ላይ ጥብቅ ህጋዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አስታውቋል።