Fana: At a Speed of Life!

ቱኒዚያውያን አዲስ በተዘጋጀው የህገ መንግስት ረቂቅ ላይ በተያዘው ሐምሌ ወር ህዝበ ውሳኔ ያደርጋሉ

አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 24 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የቱኒዚያ መንግስት በአዲስ መልኩ ያዘጋጀውን የህገ መንግስት ረቂቅ ላይ በተያዘው ሐምሌ ወር ለህዝበ ውሳኔ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡
በቱኒዚያ ለፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ የበለጠ ስልጣን ይሰጣል የተባለው እና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ሚና እንደሚገድብ የተነገረለት አዲሱ ረቂቅ ህገ መንግስት በተያዘው ሐምሌ ወር ድምጽ እንደሚሰጥበት ተመላክቷል፡፡
በሀገሪቱ የመንግስት ጋዜጣ ላይ የታተመው አዲሱ ህገ መንግስት÷ ፕሬዚዳንት ካይስ ሰኢድ አዲስ ፓርላማ እስከሚመሰረት ድረስ በስልጣናቸው እንደሚቀጥሉ የሚፈቅድ ነው ተብሏል፡፡
አዲሱ የሕገ መንግሥት ፕሬዚዳንቱ ረቂቅ ሕጎችን እንዲያዘጋጁ ከመፍቀዱ ባሻገር የሚደረጉ ስምምነቶችን የማቀድ እና የክልሎችን በጀት የማዘጋጀት ኃላፊነት በብቸኝነት የሚሰጥ መሆኑም ነው የተገለጸው፡፡
በሌላ በኩል አዲሱ ሕገ መንግስት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ “የክልሎች ምክር ቤት” የተሰኘ አዲስ ምክር ቤት ለማዋቀር የሚፈቅድ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
ይህን ተከትሎም የሀገሪቱ ተፎካካሮ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ ህገ መንግስቱን በአዲስ መልኩ ማዘጋጀታቸው ስልጣናቸውን ለማስቀጠል የወሰዱት የአንድ ወገን እርምጃ ነው በሚል ውድቅ አድርገውታል፡፡
ዜጎችም በአዲስ መልኩ ተዘጋጅቶ ለህዝበ ውሳኔ ይቀርባል በተባለው አዲስ ህገ መንግስት ላይ ድምጽ ከመስጠት እንዲቆጠቡ መጠየቃቸውን ቲ አር ቲ ዘግቧል፡፡
አዲሱ ሕገ መንግስት 10 ምዕራፎች እና 142 አንቀጾችን የያዘ እና ቱኒዚያ በፕሬዚዳንታዊ ስርአት የምትመራ ሉዓላዊ ሀገር መሆኗን የሚደነግግ ነው።
 
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
 
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.