ዓለምአቀፋዊ ዜና

በኳታር የተካሄደው የኢራን የኒውክሌር ድርድር ያለ ስምምነት ተጠናቀቀ

By Meseret Awoke

July 01, 2022

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢራንና በዓለም ሃያላን ሀገራት መካከል የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ለማደስ የተካሄደው ውይይት ግቡን ሳይመታ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

በፈረንጆቹ 2015 የተደረሰውን የኒውክሌር ስምምነት ለማደስ የተካሄደው የመጨረሻው ዙር ውይይት ብዙም ርቀት ሳይጓዝ መጠናቀቁን የአውሮፓ ህብረት አሸማጋይ ኤንሪኬ ሞራ ተናግረዋል ።

ሁለቱም ወገኖች ለተቋረጡት ድርድሮች እርስ በእርሳቸው እንደተወቃቀሱም ነው የተነገረው።

አሸማጋዩ አሜሪካ እና ኢራን “የአውሮፓ ህብረት ተስፋ ያደረገበትን ስምምነት” ማድረግ እንዳልቻሉ በመግለጽ ፥ በኳታር ዋና ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው ውይይት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በተለያየ ጊዜ የተካሄደው ድርድር ጥቂት ውጤቶች ቢያስገኝም ፥ ልዑካኑ የኒውክሌር ስምምነቱን ለማደስ “ከዚህም በበለጠ ፍጥነት መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ” ገልጸዋል።

ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ፥ ቴህራን የድርድሩ መጓተት ተጠያቂ ናት ብለዋል።

አያይዘውም እልባት ያገኙ ጉዳዮችን እንዲሁም ከ2015 የኒውክሌር ስምምነት ጋር ያልተያያዙ አዳዲስ ጉዳዮችን እንዲነሱ አድርገዋል በሚል የቴህራን ተደራዳሪዎችን ወቅሰዋል።

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፥ የአውሮፓ ህብረት አሸማጋይ የሆኑት ኤንሪኬ ሞራ በቪየና ኦስትሪያ እና በኳታር ዶሃ የተካሄደው የኒውክሌር ድርድር እንዴት መቀጠል እንዳለበት ከኢራን ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ባገሪ ካኒ ጋር መምከራቸውን እንደሚቀጥሉ መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል።

በፈረንጆቹ 2015 መጀመሪያ የተፈረመውና በመደበኛነት የጋራ አጠቃላይ የድርጊት መርሐ ግብር በመባል የሚታወቀው የኒውክሌር ስምምነቱ በኢራን የኒውክሌር ሃይል ፕሮግራም ላይ ጥብቅ ጥበቃዎችን ለማድረግ ያለመ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!