የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቆመ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት ማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተጠቆመ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ከአማራ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል፣ ጋምቤላ ክልሎች እና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለተውጣጡ 300 የኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ ባለሙያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠና በባህር ዳር ከተማ እየሰጠ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ብሩ ወልዴ በስልጠናው ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ ተቋሙ የአምራች ኢንተርፕራይዞች ዘርፍ ፈጻሚዎችንና አስፈጻሚዎችን አቅም ለመገንባት በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ በትኩረት ሲሰሩ ከቆዩ ስራዎች አንዱ የመፈጸምና ማስፈጸም አቅምን መገንባት መሆኑን ጠቁመው÷ ይህም የኢንተርፕራይዞችን ተወዳዳሪነት በማጎልበት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው መግለጻቸውን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት መረጃ ያመላክታል፡፡
አምራች ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን ተጨባጭ ችግሮች ለመለየትና የሚቀረፉበትን መንገድ አስመልክቶ በአስፈጻሚዎች ዘንድ ወጥ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖር ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ አምራች ኢንተርፕራይዞችን ለማበራከትና ኤክስፖርትና ተኪ ምርቶች ላይ በስፋት እንዲሰማሩ ለማስቻል የዘርፉ አመራርና ባለሙያዎች በትጋት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ታረቀኝ ለዘርፉ ውጤታማነት ብቃት ያለው አመራርና ባለሙያ ሚና የጎላ በመሆኑ÷ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!