የሀገር ውስጥ ዜና

የአንድን ቻይናዊ ሕይወት በማጥፋት ወደ ኬንያ የሸሹ ተጠርጣሪዎች ለኢትዮጵያ ተላልፈው ተሰጡ

By ዮሐንስ ደርበው

July 01, 2022

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ዳይሬክተር ኮማንደር ፀጋዬ ሀይሌ እንደተናገሩት ÷ ሁዋንግ ዥፔንግ ፣ ሊቭ ጄ ፣ ዋንግ ሚንግ እና ቻ ኦ ፉ ሲዛኦንግ የተባሉት አራት ተጠርጣሪዎች ወንጀሉን ከፈፀሙ በኋላ ወደ ኬንያ አምልጠዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኢንተርፖልም ከአዲስ አበባ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ምርመራውን በፍጥነት በማካሄድ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ዓለም አቀፍ የኢንተርፖል ቀይ ማስታወቂያ አውጥቶባቸው ሲፈለጉ እንደነበር ነው ዳይሬክተሩ ያወሱት፡፡

ለ24 ሰዓት በተደረገ የመረጃ ልውውጥ ኬንያ መግባታቸው በመረጋገጡ÷ ከኬንያ ብሔራዊ ኢንተርፖል ጋር በጥምረት በመስራት ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ኮማንደር ፀጋዬ፡፡

አራቱም ቻይናውያን ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ወንጀል ፈፅመዋል ተብለው ወደ ተጠረጠሩበት ኢትዮጵያ ገብተው ምርመራ እንዲጣራባቸው ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ተላልፈው ተሰጥተዋል ማለታቸውምን የፌደራል ፖሊስ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዳይሬክተሩ አክለውም ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከሕግ ማምለጥም ሆነ መደበቅ እንደማይችል በዓለም አቀፉ የፖሊስ ኀብረት ኢንተርፖል ተፈልጎ ሕግ ፊት የሚቀርብ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።