Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ ሊፈቱ ይገባል – ደቡብ ሱዳናዊ ምሁር

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን ከውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነፃ በሆነ መልኩ በውይይት ሊፈቱ እንደሚገባ የጁባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ቴር ቶኚክ ማጆክ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የድንበር ውዝግቡን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተደጋጋሚ ጥረት ብታደርግም÷ የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ችግሩን ለማባባስና ዓለም አቀፋዊ ለማድረግ መሞከሩ ተገቢ አመሆኑን ነው ረዳት ፕሮፌሰር ቴር ያስረዱት፡፡

ቅኝ ገዥዎች በአፍሪካ በነበራቸው የወረራ ዘመን ሀገራትን ሊያጋጭ የሚችል የድንበር ችግር ትተው መሄዳቸውን ጠቁመው÷ ያም ሆኖ የድንበር ውዝግቡን ሁለቱ ሀገራት የመፍታት አቅም እንዳላቸው አመላክተዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአፍሪካ ኀብረት እና የኢጋድ አባል እንደመሆናቸው÷ በተለይም ሌሎች ጎረቤት ሀገራት ኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ውዝግባቸውን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት ረዥም የወዳጅነት ታሪክ እንዳላቸው ያስታወሱት ረዳት ፕሮፌሰር ቴር÷ የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ ጣልቃ ለመግባት ለሚሞክሩ የውጭ ኃይሎች ጆሮ መስጠት እንደሌለባቸውም መክረዋል፡፡

ታሪካዊ ወዳጅነታቸውን በማሰብ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት እንዳይኖር በማድረግ በሁለቱ ውይይት ብቻ የሚቋጭ መፍትሔ ሊዘረጉ ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት አማራጩ ሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆን እንዳለበት ያመላከቱት ረዳት ፕሮፌሰሩ÷ የተባበሩት መንግስታት ቻርተር የትኛውም ሀገር በሌሎች ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት እንደሌለበት በማስታወስ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የጋራ ጉዳያቸውን እራሳቸው ብቻ ሊጨርሱት እንደሚገባና እንደሚችሉ ነው የመከሩት፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.