Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት የህዝብ አንድነት እንዲሸረሸር በሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግሥት የህዝብ አንድነትና አብሮነት እንዲሸረሸር በሚያደርጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የመገናኛ ብዙሃን ላይ እርምጃ እንደሚወስድ አስታወቀ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ በህዝባዊ መድረኮችና መገናኛ ብዙሃን በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮች በሃገር አንድነትና አብሮነት ላይ አደጋ ይደቅናሉ።

ከዚህ አንጻርም በመሰል ድርጊት በሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የመገናኛ ብዙሃን ላይ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ጋር በመሆን ተገቢና ተመጣጣኝ ዕርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድ አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም በትናንትናው ዕለት ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በተመለከተ በአዲስ አበባ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኦፌኮ) ባዘጋጀው መድረክ በ”ኦ ኤም ኤን” (OMN) አማካኝነት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌን የጣሰና ኢትዮጵያዊ ዕውነታን ያላገናዘበ የጥላቻ ንግግር ለዘመናት በአብሮነት ወደኖሩ ህዝቦች መተላለፉን ተከትሎ ፓርቲውም ሆነ የመገናኛ ተቋሙ ተገቢውን ኃላፊነት መውሰድ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የተፈጠረው ነገር ስህተት ብቻ ሳይሆን ጥፋት መሆኑንም አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።

አቶ ንጉሱ መንግሥት ለረጅም ጊዜ በመማማርና መመካከር ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴን አማራጭ አድርጎ በትዕግስት መቆየቱን አንስተዋል።

አሁን ግን በሃገሪቱ ላይ ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ተግባራት በግልፅ እየተበራከቱ በመምጣታቸው መንግስት እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር ነው የገለፁት።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንና ብሄራዊ ምርጫ ቦርድም በዚህ ረገድ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን በፍጥነት እንዲታረሙ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አውስተዋል።

በሶዶ ለማ እና ትዕግስት ስለሺ

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.